ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለውን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለውን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራ ነው
አዳማ፤ መስከረም 30/2019(ኢዜአ )፡-የኦሮሚያ የሕግ ስልጠናና ምርምር ኢንስቲትዩት ጥራት ያለውን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በሕግ ክህሎትና ስነ ምግባር የታነጹ ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራ መሆኑን አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ረዳት ዐቃቤ ሕጎችና ጠበቆችን ዛሬ አስመርቋል ።
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮ ሃላፊ አቶ ጉዮ ዋሪዮ እንደገለፁት የክልሉን የፍትህ ስርዓት ሪፎርም ለማሻሻልና ውጤታማ ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ተግባር ኢንስቲትዩቱ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል።
በተለይ የፍትህ ስርዓቱን ስነ ምግባርና ብቃት ባላቸው የሰው ሃይል ለመምራት ከስልጠና በተጓዳኝ በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለማህበረሰቡ ጥራት ያለውን የፍትህ አገልግሎት መስጠት የሚቻለው ሙያዊ ስነ ምግባርና እውቀት ያለው የሰው ሃይል ማፍራት ነው ብለዋል።
በመሆኑም የዛሬው ምሩቃን ያገኙትን ዕውቀት ሥራ ላይ በማዋል ማህበረሰቡን በሥነምግባርና በታማኝነት ማገልገል አለባቸው ብለዋል።
ራሳቸውን ዘመኑ ከሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ጋር በማዋሃድ ክህሎትና ብቃታቸውን ማጎልበትና የተሻለ ደረጃ ላይ መገኘት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አዱኛ አህመድ በበኩላቸው ተመራቂዎች በቀጣይ ወደሥራ ሲሰማሩ ህዝብን በፍትሃዊነት በቅንነት ማገልገል አለባቸው ብለዋል።
በተለይ ስነ ምግባርና የአገልጋይነት መንፈስ በመላበስ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ያሉት ዳይሬክተሯ ኢንስቲትዩቱ ከስልጠና በተጓዳኝ ለክልሉ የፍትህ ሪፎርም ማሻሻያ ወሳኝ ግብዓት የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።
በተለይ ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎችና ጠበቆች ተገቢውን ስነ ምግባርና ዕውቀት እንዲላበሱ ከማድረግ ባለፈ ብቁ የህግ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተም ይገኛል ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ቀነኒ በበኩላቸው እንዳሉት ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን የህግ ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር ሊቀይሩ ይገባል።
ሙያዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣትም የህብረተሰቡን የፍትህ አገልግሎት ጥራትና የተደራሽነት ጥያቄ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በስነ ምግባርና በአገልጋይነት መንፈስ ህዝብን በሙሉ አቅማቸው ማገልገል እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።