የሠመራ ጤና ሳይንሰ ኮሌጅ 239 የህክምና ተማሪዎችን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሠመራ ጤና ሳይንሰ ኮሌጅ 239 የህክምና ተማሪዎችን አስመረቀ
ሰመራ፣ መስከረም 30/2019(ኢዜአ) ፡-የሠመራ ጤና ሳይንሰ ኮሌጅ ለ14ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 239 የህክምና ተማሪዎችን አስመረቀ።
በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አህመድ ኢብራሂም፤ የተመረቁት የጤና ባለሙያዎች የክልሉን የጤና አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነቱን ለማስፋት አስተዋጽኦ የሚኖራቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የህክምና ባለሙያዎቹ ህዝባቸውን በቅንነትና በታታሪነት በማገልገል ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ያሲን ሀቢብ፤ ተመራቂዎች የክልሉን ህዝብ የጤና አገልግሎት ለማሻሻልና ህዝባቸውን ለማገልገል መትጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የዋንጫና ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆን በከፍተኛ ማእረግ የተመረቀው አሊ ኢብራሂም፤ በተመረቀበት የክሊኒካል ነርስ ሙያ በቅንነት፣ በታታሪነትና በታማኝነት ለማገልግል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ሌላኛዋ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀችውና የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነቸው ዘሀራ መሐመድ አደን፤ በህክምና ሙያ ህዝብን ማገልገል መታደል መሆኑን በማንሳት ሙያዊ ሃላፊነቷን በብቃት የምትወጣ መሆኑን ተናግራለች።