የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትና እና የገቢ ምንጭ በመሆን ኑሯችንን ለውጧል - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትና እና የገቢ ምንጭ በመሆን ኑሯችንን ለውጧል
ደብረ ብርሃን ፤መስከረም 30/ 2019 (ኢዜአ) ፡-የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትና እና የገቢ ምንጭ በመሆን ኑሯችንን ለውጧል ሲሉ በደብረ ብርሃን በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በመንግስት አዳዲስ ኢንሼቲቮች የሚደገፈው የግብርናው ዘርፍ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የበርካታ አርሶና አርብቶ አደሮች ህይወት ላይ በተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ የእንስሳት እርባታ፣ የአረንጓዴ አሻራና ሌሎችም በመንግስት በትኩረት እየተሰሩና እየተደገፉ የሚገኙ የልማት ስራዎች ብዙዎችን ውጤታማ አድርገዋል።
በመሆኑም በደብረ ብርሃን ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እየተሳተፉ ያሉ አልሚዎች፤ የምግብ ዋስትና መሰረት ይዘናል የህይወት ለውጥም አምጥተናል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ገብርየ ከበደ እና አርሶ አደር ጌታቸው ሸዋፈራ፤ በሌማት ትሩፋት ከቤተሰብ ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በእንስሳት እርባታና የወተት ልማት ድጋፍ ተደርጎላቸው ውጤታማ በመሆናቸው የገበያ ትስስር በመፍጠር በየእለቱ የገቢ ምንጭ እያገኙ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
የመስሪያ ቦታ፣ የብድር አቅርቦት ተመቻችቶላቸው በስልጠና ጭምር ታግዘው ለውጤት መብቃተቸውንም አልሚዎቹ አስታውሰዋል።
ሌላው አርሶ አደር ምትኩ ጌታቸው፤ በመደበኛ እና በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት በተከታታይ እያመረቱ በመሆኑ ከራሳቸው ፍጆታ ያለፈ ምረት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የበጋ መስኖ ልማት ስራቸውን አጠናክረው በመቀጠል የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የደብረ በርሃን ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ መርሻ ዓይሳነው፤ በከተማዋና አካባቢው በሌማት ትሩፋትና የበጋ መስኖ ልማት የርካታ አርሶ አደሮች ህይወት እየተለወጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በእንስሳት ማድለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በወተትና እንቁላል እንዲሁም የማር ምርት አበረታች ውጤት መጥቷል ብለዋል።
የበጋ መስኖ የስንዴ ልማትም አሁን ላይ 4 ሺህ 200 ሄክታር መድረሱን ጠቁመው በቀጣይም የልማት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።