ለሰላም ለአብሮነትና ለልማት መጠናከር የድርሻችንን እንወጣለን - የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላም ለአብሮነትና ለልማት መጠናከር የድርሻችንን እንወጣለን - የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች
ሀዋሳ፤ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ) ፦ለህዝቦች ዘላቂ ሰላምና አብሮነት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ በማስቀጠል የመንግስት የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ በተካሄደው የመደመር መንግስት ምስረታ ወቅት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የመንግስት ዋና ዋና የልማት ትኩረቶች ለህዝብ ይፋ መደረጋቸው የሚታወስ ነው።
በዚህም ሰላም ማጽናት፣ መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ፣ መሰረተ ልማትን ማስፋፋትና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶችን ማስቀጠል ከመንግስት የትኩረት ግቦች ይጠቀሳሉ።
በመንግስት ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች እንደተናገሩት፤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እንዲሳኩ ዘላቂ ሰላምና የህዝቦች አብሮነትን ማጠናከር ወሳኝ ነው።
የልማትና የእድገት ግቦቹ በህዝብ ዘንድ ተስፋን የሰነቁ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በመደመር መንግስት የተያዙ ሁለንተናዊ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ለዘላቂ ሰላምና ለህዝቦች አብሮነት አበክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ከሲዳማ ሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ሻምበል በላይ እንደገለጹት፣ አዲስ የተመሰረተው መንግስት የህዝቦችን አንድነትና ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ ያስቀመጣቸው ግቦች የሚሳኩት በህዝብ ትብብር ሲሰራ ነው፡፡
በየአካባቢው የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ አብሮነቱን እንዲያጠናከር ሚናዬን እወጣለሁ ብለዋል።
ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ ቦና ቦቆንቻ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግስት አዳዲስ የልማት አቅጣጫዎችና ግቦች ህዝቡ ተስፋን እንዲሰንቅ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ሰላም፣ ልማትና የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር የተጀመሩ ሥራዎች ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ በመደመር መንግስትም እነዚህ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
የተያዙ የልማት ግቦች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ ባህላዊ የሰላም እሴቶችን በማጎልበት የህዝብን አንድነት የማጠናከር ሃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
በሲዳማ ብሔር ባህላዊ የግጭት አፈታትና የዳኝነት ሥርአት አስታራቂ ሽማግሌ የሆኑት ሻለቃ ጨመረ ሻልኬ በበኩላቸው፣ በቀጣይ ሀገራዊ ለውጥ የሚያመጡ አዳዲስ አቅጣጫዎች በመንግስት መቀመጣቸው የሚደገፍ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በከተማና በገጠር የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም እነዚህ እንዲጠናከሩ ከመንግስት ጎን ሆነው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በተለይ በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው ህዝብን ለሰላምና ለልማት ለማስተባበር ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለጹት