ቀጥታ፡

የፍርድ ቤቶች በዲጂታል የታገዘ አሰራርን መከተል የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል

ባህር ዳር፤ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ) ፦ የፍርድ ቤቶች በዲጂታል የታገዘ አሰራርን መከተል ተቋማዊ ነጻነትን በማስጠበቅ ቀልጣፋና ተአማኒ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት ማስቻሉን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት ገለጹ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በዲጂታል አሰራር ታግዞ በተተገበረው የፍርድ ቤቶች ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ላይ የመከረ ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች ጉባኤ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

በጉባኤው ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት እንደገለጹት፣ የፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ላለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ ሆኗል።

ፎኖተ ካርታው ለዲጂታል አሰራር ትኩረት በመስጠቱ ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ ነጻነታቸውን አስጠብቀው ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና በህዝብ ዘንድ እርካታን የፈጠረ የፍትህ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ይህም የዳኝነት ሥርአቱን ከነበረበት ኋላ ቀር አሰራር በማውጣት ዘመኑን የሚመጥን የህግና የፍትህ አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመስጠት አበረታች ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል ብለዋል።

በቀጣይም በሁሉም ክልሎችና አካባቢዎች የዲጂታል ሥርአት ዝርጋታን በማፋጠን ተቀራራቢ የሕግ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የዛሬው ሀገራዊ የህግ ተርጓሚዎች ጉባኤም ባለፉት ዓመታት የመጡ ለውጦችን አሻሽሎ ለማስቀጠልና የተስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጎልበት ያለመ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አለምአንተ አግደው በበኩላቸው እንዳሉት፣ የክልሉ የዳኝነት ሥርዓት ዘመኑን የሚመጥን ለማድረግ በዲጂታላይዜሽን አሰራር ላይ በማተኮር  እየተሰራ ይገኛል።


 

በዚህም ዜጎች ፍትህ ፍለጋ መንከራተት ሳያስፈልጋቸው እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሰጡ የፍትህ አገልግሎቶችን በአካባቢያቸው ሆነው የሚያገኙበት ሥርአት መዘርጋቱን አስታውቀዋል።

ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች ጉባኤም ድንበር የለሽ የሕግ አገልግሎት ለመስጠትና አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ያስችላል ብለዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ከሌሎች አቻ የሀገሪቱ የፍትህ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው መድረክ ከሁሉም ክልሎች የመጡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም