ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አመታት ጥሬ ዕቃዎችን በማቀነባበር እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች የማስገባት ልምዷን ትገታለች-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት እና አስር ዓመታት ውስጥ በጥሬ ዕቃ መልክ የምትልካቸውን ምርቶች እሴት በመጨመር፣ ከውጭ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች የማስገባት ልምዷን በደረጃ እንደምትገታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የመደመር ግራንድ ስትራቴጂ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃዎቿን በአነስተኛ ዋጋ ልካ መልሳ በከፍተኛ ዋጋ የተዘጋጁ ምርቶችን የምትገዛበትን አሰራር ለማስቀረት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በዓመት እስከ 80 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ኤክስፖርት የማድረግ አቅም እንዳለውም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ተገንብቶ ሥራ የጀመረው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ሥራ አስጀምረዋል።

ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አጋርነት የተቋቋመ መሆኑ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት እና አስር ዓመታት ውስጥ በጥሬ ዕቃ መልክ የምትልካቸውን ምርቶች እሴት በመጨመር፣ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ከውጭ የማስገባት ልምዷን በደረጃ ትገታለች።

የመደመር ግራንድ ስትራቴጂ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃዎቿን በአነስተኛ ዋጋ ልካ መልሳ በከፍተኛ ዋጋ የተዘጋጁ ምርቶችን የምትገዛበትን አሰራር ለማስቀረት መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ጥጥ፣ ቡናና ወርቅ የመሳሰሉ ጥሬ ዕቃዎችን በዝቅተኛ ዋጋ ከላከች በኋላ፣ ተቀነባብረው ወደ አፍሪካ ገበያ በብዙ እጥፍ ዋጋ ተመልሰው እንደሚሸጡ ተናግረዋል።

ለአብነትም በአዲስ አበባ በ8 ዶላር የሚሸጥ ቡና በውጭ ሀገር ተቆልቶና ተዘጋጅቶ በስታርባክስ ከ30 ዶላር በላይ፣ በጣሊያን ደግሞ ወደ ኤስፕሬሶ ተቀይሮ እስከ 50 ዩሮ እንደሚሸጥ አንስተዋል።

ይህ አሰራር በወርቅ ብቻ ሳይሆን በማዳበሪያና በሌሎች ቁልፍ የማዕድን ዘርፎችም ተተግብሮ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ አብራርተዋል።

ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በዓመት እስከ 80 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ኤክስፖርት የማድረግ አቅም እንዳለው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን ሰፊ ተደራሽነት አቅምን በመጠቀም ከሀገር ውስጥ አልፎ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚወጣውን ወርቅ በማሰባሰብና በማጣራት ትልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይፈጥራል ብለዋል።

በወርቅ ዘርፍ ባለፈው ዓመት ከተላከው ከ5 እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ውስጥ ይህ የማጣሪያ አቅም ቀደም ብሎ ቢኖር ገቢው እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል 1 ኪሎ ወርቅ ሲላክ 70 በመቶው ብቻ ወርቅ ተብሎ ቀሪው 30 በመቶ እንደ ቆሻሻ ይደፋ ነበር፤ የሚደፋው አካል እንደ ብር ያሉ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ማዕድናት ያካተተ ነው ብለዋል።

በአዲሱ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካም ከፍተኛ ጥቅም እንደሚገኝበት አብራርተዋል።

ይህን ማጣሪያ ፋብሪካ የሚያንቀሳቅሱትና የሚያስተዳድሩት በዘርፉ የሰለጠኑ ሀገር በቀል ባለሙያዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም