በኦሮሚያ ክልል በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና እና ሽልማት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና እና ሽልማት ተሰጠ
ቢሾፍቱ ፤መስከረም 30/2019 /ኢዜአ/፡-በኦሮሚያ ክልል በ2018 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና እና ሽልማት ተሰጠ።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በቢሾፍቱ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ ዕውቅና እና ሽልማቱ የተሰጠው በ2018 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ550 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ 165 የተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ነው።
ለተማሪዎቹ የገንዘብ ሽልማትና ሰርተፊኬት የሰጡት የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አብዱሰላም ዋሪዮ እና የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቡልቶሳ ሂርኮ (ዶ/ር) ናቸው።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቡልቶሳ ሂርኮ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት እና ጥራቱን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።
በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ 19 ሺህ 352 የኢፋ ቦሩ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በገጠርና በከተማ በመገንባት በደረጃው የትምህርት ተደራሽነትን ማረጋገጥ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የተማሪዎች የማንበብ፣ የመፃፍና የማስላት ክህሎት ለማሳደግ እንዲቻል ከውጭ ሀገር ተሞክሮ በመውሰድና 59 ሺህ መምህራንን በማሰልጠን በ13 ሺህ 293 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በማሰማራት አበረታች ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።
በክልሉ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎችን ቁጥር ለማሳደግም ሰባት ብቻ የነበረውን ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር ባለፉት ጥቂት አመታት ወደ 46 ማስፋፋት መቻሉን አስታውቀዋል።
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የከተማና የገጠር መምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል የክልሉ መንግስት መስራቱንም አስታውቀዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀዋል።
ዛሬ እውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው ተማሪዎች በርትተው በመስራት ለውጤት መብቃታቸውን ጠቁመው ተምሳሌታቸውም ለሌሎች ተማሪዎች መነሳሳት እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
ተሸላሚ ተማሪዎች ይህ የመጨረሻ ስኬት ሳይሆን የመጀመሪያ ምእራፍ መሆኑን በመገንዘብ በቀጣይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በስነምግባር ታንፀው ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ለተሻለ ውጤት እንዲተጉ አሳስበዋል።
ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ከተሸለሙት መካከል ከማያ ከተማ ሀረማያ ቦርዲንግ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ ሀምዛ መሀመድ በሰጠው አስተያየት በተፈጥሮ ሳይንስ 576 ነጥብ ማምጣቱን ተናግሯል።
ውጤቱን ተከትሎ የተሰጠኝ ሽልማትና እውቅና በቀጣይ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቆይታዬ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መነሳሳትና የሞራል ስንቅ ይሆነኛል ብሏል።
በዕውቅና እና ሽልማት ስነ ስርአቱ ላይ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የተማሪ ወላጆች ተገኝተዋል።