ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በትምህርት ዘርፍ በቅንጅት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ተገኝቷል

ቢሾፍቱ ፤መስከረም 30/2019 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ  ክልል በትምህርት ዘርፍ በቅንጅት በተከናወኑ ተግባራት  አበረታች ውጤት መገኘቱን የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2018 ትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ እውቅናና ሽልማት አበርክቷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት  የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንዳስታወቁት  የክልሉ መንግስት  የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ቋሚ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

በዚህም አበረታች ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው በቀጣይ ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

በተለይ የትምህርት ጥራትን ከታችኛው እርከን አንስቶ ለማረጋገጥ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት  በመንግስትና በህዝብ  በተደረገው ርብርብ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ህፃናት የትምህርት ተደራሽነትን ማረጋገጥ መቻሉን አንስተዋል።

የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በክልሉ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት በየአመቱ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎችን ቁጥር ማሻሻል መቻሉን አመልክተዋል።

ትምህርትና ቴክኖሎጂ ለሀገር ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግስት በቀጣይ በየደረጃው የሚሰጠው ትምህርት  ከቴክኖሎጂ ጋር የሚጣጣምና ችግር ፈቺ እንዲሆን አበክሮ ይሰራል ብለዋል።


 

እንዲሁም  የክልሉ መንግስት  በገጠርና በከተማ በተለያየ እርከን  የትምህርት ተደራሽነትን፣ ጥራትን እና ብቃትን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

ዛሬ ለሽልማት የበቁ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ጠንከረው በመትጋታቸው ያመጡት ውጤት ስለሆነ የክልሉ መንግስት ያበረታታል፤ በቀጣይም ከጎናቸው ይቆማል ብለዋል። 

በዩኒቨርስቲ ቆይታቸውም በማናቸውም ሁኔታ ሳይበገሩ በርትተው በመስራት ለሀገራቸው ኩራት መሆን እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

የትምህርት ባለድርሻ አካላትም የትምህርት ጥራትን ይበልጥ ለማሻሻል እንዲሁም  የዘርፉን አሠራር ለማዘመን እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎችን በማጠናከር የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እንዲተጉ አሳስበዋል።

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በቢሾፍቱ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ በ2018 የትምህርት ዘመን  በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ550 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ 165 የተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ  ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።
 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም