የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ትንሳኤ፦ከትላንት መዋቅራዊ ፈተናዎች እስከ ቀጣናዊ ማዕከልነት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ትንሳኤ፦ከትላንት መዋቅራዊ ፈተናዎች እስከ ቀጣናዊ ማዕከልነት
የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ሰፊ እምቅ አቅም ቢኖረውም፣ ሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል መጠቀም ሳትችል ቆይታለች።
ከዚህ ቀደም ዘርፉ በዋናነት በባህላዊ እና አነስተኛ አምራቾች ላይ የተንጠለጠለ፣ በህገ-ወጥ ኮንትሮባንድ ንግድ የተተበተበ፣ እንዲሁም ጥሬ ማዕድናትን ያለምንም እሴት በቀጥታ ወደ ውጭ በመላክ ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር።
ይህ ዓይነቱ አሠራር ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ ከማሳጣቱ ባለፈ፣ የማዕድን ዘርፉ ለአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ያለው አስተዋፅኦ ከአንድ በመቶ በታች ሆኖ እንዲቀጥልና ለኢንዱስትሪው ልማት የሚጠበቀውን ግብዓት እንዳያበረክት ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ዘርፉን ለማዘመንና የአገር ውስጥ አቅምን ለማሳደግ ስትራቴጂካዊ የፖሊሲ እና የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ (Sam Precious Metals) ዓለም አቀፍ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ መመረቁን ያበሰሩት ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ የዚህ ሪፎርም ትልቅ ማሳያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፋብሪካው፤ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር፣ የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ ለማጠናከር እና ሀገራችንን በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ረገድ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
ይህ ውጥን፤ ሀብቶቻችንን ከኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማስተሳሰር ወጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ይበልጥ ግልጽ እና ተወዳዳሪ የሆነ የወርቅ እሴት ሰንሰለት ለመገንባት የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ይህ ፋብሪካ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር፣ የወርቅ ጥራትን የመለካት እና የወርቅና የብር ጡቦችን የማምረት ሙሉ አቅም ያለው በመሆኑ፣ አገሪቱ ጥሬ ማዕድናትን ዝም ብሎ ከመቆፈር ባለፈ እሴት ጨምራ እንድታመርት የሚያደርግ ነው።
በማዕድን ዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ስኬት በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እና የብዝሃ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ አዲስ ምሰሶ ሆኖ መጥቷል።
በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ከማዕድን ኤክስፖርት ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 5.65 ቢሊዮን ዶላሩ የተገኘው ከ44 ቶን በላይ ወርቅ ወደ ውጭ በመላክ ነው።
ወርቅ በአሁኑ ወቅት የላቀ የወጪ ንግድ ገቢ እያስገኘ ሲሆን፣ በሌላ በኩል እንደ ከሰል ያሉ ማዕድናት በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲታጠቡና እንዲመረቱ መደረጉ ከዚህ ቀደም ለከሰል ግዢ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን አስችሏል።
ይህም ዘርፉ ከውጭ ምንዛሬ አመንጪነት ባሻገር የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እና የጌጣጌጥ ዘርፉን የሚደግፍ ጠንካራ የኢኮኖሚ ምሰሶ እንዲሆን አድርጎታል።
የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ መጻኢ ጊዜ እጅግ ብሩህና ተስፋ ሰጪ በሆኑ ስኬቶች የተሞላ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል።
መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አማካኝነት፣ የማዕድን ዘርፉ ለሀገር ውስጥ ምርት የሚያበረክተውን ድርሻ ወደ 10 በመቶ ለማሳደግ እየሰራ ነው።
በ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት ከዘርፉ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።
እንደ ቱሉ ካፒ እና ኩርሙክ ያሉ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ደረጃ የወርቅ ማውጫ ፕሮጀክቶች ወደ ሙሉ ሥራ መሸጋገራቸው ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
አዲሱ የብሔራዊ ውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በወርቅ ዋጋ አተማመን ላይ ግልጽነትን፣ የጥራት ማረጋገጫንና እምነትን በማስፈን ይህንን ታላቅ ጉዞ በጽኑ መሠረት ላይ የሚያስቀምጥ ነው።
ይህ ፋብሪካ ኢትዮጵያን በጥሬ ማዕድን አቅራቢነት ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ ገበያዎች ሰፊ ዕድሎችን የምትፈጥር የምሥራቅ አፍሪካ የውድ ማዕድናት ማቀነባበሪያ ዋና ማዕከል የሚያደርጋት ነው።