ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ ልማት የሰጠው ትኩረት በዘርፉ ያሉ ሀብቶች ለዓለም እንዲተዋወቁ ዕድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ ልማት የሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ለዓለም ለማስተዋወቅ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለፁ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የመደመር መንግሥት ከለያቸው ዋና ዋና የልማት ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ በመሆኑ፣ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሀብቶችን በማልማት የኢኮኖሚ ምንጭነታቸውን ለማጎልበት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በተጨማሪም በቱሪዝም ዘርፉ ያሉ እምቅ ሀብቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና የሀገር ውስጥ ገጽታን ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያ ያሏትን ታሪካዊ ቅርሶችና ቱባ ባህል ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

አቶ ውብአንተነህ ብሩ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፣ ቱሪዝም የአንድን ሀገር ቅርስና ባህል ለተቀረው ዓለም የሚያስተዋውቅበት ሰፊ መድረክ መሆኑን ጠቁመው፣ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የሰጠው ትኩረት ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚገኙ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ሀብቶች ይበልጥ ሳቢና ታሪክ ነጋሪ እንዲሆኑ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ባከናወናቸው ተግባራት ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶችና ታሪክ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ፣ ብሎም ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦውን ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ እመቤት ማስረሻ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ቁጥር መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የቱሪዝም ዘርፉን በላቀ መልኩ በማልማት፣ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበኩሉን እያበረከተ መምጣቱን አብራርተዋል።

አቶ መላኩ ገብረየስ እንደሚናገሩት፣ ባለፉት ዓመታት መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት በመስጠት በተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት፣ በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ከመሠረታቸው ለማቃለል ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።


 

ይህ የመንግሥት ትኩረት ሀገሪቱ ከዘርፉ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንድታገኝ እያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወይዘሪት መሠረት እንዳለ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፣ በመላ ሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንድታገኝ፣ በዘርፉ የተከናወኑና እየተከናወኑ የሚገኙ የመዳረሻ ልማቶችን የማስተዋወቅ ሥራ ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉት ጥረት መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም