የሕክምና ኦክሲጅን ተደራሽነትን የማስፋፋት ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕክምና ኦክሲጅን ተደራሽነትን የማስፋፋት ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እያስቻለ ነው
ድሬዳዋ፤ መስከረም 30/2019(ኢዜአ):-በጤና ሚኒስቴር የተጀመረው የሕክምና ኦክሲጅንን ተደራሽነት የማስፋፋት ሥራ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕውን ለማድረግ እያስቻለ መሆኑ ተገለጸ።
ዓለም አቀፍ የኦክሲጅን ግንዛቤ ማሳደጊያ ቀን በድሬዳዋ የኦክሲጅን ማምረቻ ማዕከልን (ፕላንት) በመመረቅና በተለያዩ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች እየተከበረ ነው።
በድሬዳዋ በድል ጮራ ሆስፒታል ሥር በሚገኘው የፈረንሳይ ድንገተኛ ሕክምና ማዕከል የተገነባው ዘመናዊ የሕክምና ኦክሲጅን ማምረቻ ማዕከል (ፕላንት) ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ኢሊባቦር ቡኖ በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ መንግስት በመላው አገሪቱ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት አበረታችና ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗዋል።
የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ከሚያረጋግጡት ወሳኝ ተግባራት መካከል አንዱ የሕክምና ኦክሲጅን አቅርቦትና ምክንያታዊ የኦክሲጅን አጠቃቀም ነው።
ይህም ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጎለብት ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈፃሚው ዶክተር ኢሊባቦር፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከኮቪድ-19 በፊት የሕክምና ኦክሲጅን ማምረቻ ማዕከላት 3 ብቻ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት የማዕከላቱን ቁጥር ወደ 85 ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፣ የሕክምና ኦክሲጅን ግብአት ማኔጅመንትን ለማሻሻል የተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ ማድረጉን አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት የሕክምና ኦክሲጅንን ተደራሽነት ለማስፋፋት የተከናወነው ተግባር ጥራቱን የተጠበቀ የሕክምና አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕውን ለማድረግ እያስቻለ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የድሬዳዋ አስተደዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደን በበኩላቸው የኦክሲጅን ማምረቻ ማዕከሉ ወደ አገልግሎት መግባቱ ብሔራዊ የጤና ስርአትን ለማዘመንና ዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻላል ብለዋል።
ማዕከሉ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ መግባቱ በድንገተኛ አደጋ፣ በጽኑ ህሙማን እንክብካቤ፣ በወሊድና በከባድ ቀዶ ሕክምና ላይ የሚገኙ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ያስችላል ብለዋል።
ማዕከሉ ኦክስጅንን ማምረት መጀመሩ በኦክሲጅን እጥረት ምክንያት አንድም ሰው እንዳይሞት ያግዛል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዩሱፍ መሐመድ ናቸው።
የኦክሲጅን ማምረቻ ማዕከሉ በምርቱ የድሬዳዋ ተጎራባች ክልሎች ጤና ተቋማትን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የኦክሲጅን የግንዛቤ ማሳደጊያ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ሲሆን በሥነስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስቴር እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል
ዓለም አቀፍ የኦክሲጅን ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ4ተኛ ጊዜ፤ በአገራችን ደግሞ ለ3ተኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።