ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30 /2018 (ኢዜአ)፦ 17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ዛሬ በሩዋንዳ ኪጋሊ ይጀመራል።

በማጣሪያው ላይ ዘጠኝ ሀገራት በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከዩጋንዳ እና ብሩንዲ ጋር ተደልድላለች።

በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥቅምት 2 ከብሩንዲ እና ጥቅምት 4 ከዩጋንዳ ጋር የምድብ ጨዋታዎቹን ያደርጋል።

አዘጋጇ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን በምድብ አንድ የሚገኙ ሀገራት ናቸው።

ታንዛንያ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ በምድብ ሶስት ተደልድለዋል።

የማጣሪያ ውድድሩ ዛሬ በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያገኛል።

በምድብ አንድ አዘጋጇ ሩዋንዳ ከደቡብ ሱዳን ምሽት 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

በምድብ ሶስት ታንዛንያ ከኬንያ ከቀኑ 10 ሰዓት እና በምድብ ሁለት ዩጋንዳ ከብሩንዲ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2019 ዓ.ም ይቆያል።

በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ ሀገራት ሴካፋ ዞንን ወክለው በአፍሪካ ዋንጫ ይሳተፋሉ።

17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም