በክልሉ የተያዙ እቅዶች ለታለመው ግብ እንዲበቁ በተደመረ አቅም መስራትና ማሳካት ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተያዙ እቅዶች ለታለመው ግብ እንዲበቁ በተደመረ አቅም መስራትና ማሳካት ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ)፡- በሁሉም ዘርፎች የተያዙ እቅዶች ለታለመው ግብ እንዲበቁ በተደመረ አቅም መስራትና ማሳካት ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባው የመንግስት እና የፓርቲ የቀጣይ መቶ ቀናት ዕቅድን በማስመልከት እየመከረ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ እቅዶች በአግባቡ ወደ መሬት ወርደው በአፈጻጸምና በተጨባጭ ውጤት በህዝብ ግምገማ ጭምር ውጤታቸውና ትግበራቸው የሚለካ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በቀጣይ 100 ቀናት ለመተግበር የተያዙ እቅዶች በሁሉም የአስተዳደር ዕርከን በወጥነት ለታለመው ግብ ስኬት በተደመረ አቅም መስራትና ማሳካት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለህዝብ በተገባው ቃል መሰረት የመልካም አስተዳደር፣ የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ እና ሌሎችም ጥያቄዎችን ለመመለስ መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የክልሉን እምቅ ሃብት በማልማት ለዜጎች የሚታይና የሚጨበጥ ጥቅም እንዲሰጥ በየደረጃው ያለው አመራር በቁርጠኝነት መስራት የሚጠበቅበት መሆኑንም አስገንዝበዋል።