መንግሥት ያስቀመጣቸውን የሰላምና የልማት አቅጣጫዎች ለማሳካት የበኩላችንን እንወጣለን - አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ያስቀመጣቸውን የሰላምና የልማት አቅጣጫዎች ለማሳካት የበኩላችንን እንወጣለን - አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች
ሸገር፣ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ) ፦ በመንግሥት የተቀመጡ የሰላምና የልማት አቅጣጫዎችን ለማሳካት በሚደረግ ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሸገር ከተማ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች፤ መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከአባ ገዳዎች መካከል አባ ገዳ ቶሊ ኤግዱ እንደገለጹት፤ መንግሥት የሰላምና የልማት አቅጣጫዎችን ለማሳካት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።
በተለይም በገዳ ሥርዓት እሴቶች መሠረት ለትውልዱ ፍቅርን፣ አንድነትንና ሰላምን በማስተማር ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡም ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የልማትና የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር በጋራ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ሃደ ሲንቄ ካባ በያና በበኩላቸው፤ ሰላም የሁሉም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች መሠረት መሆኑን ጠቁመው፣ "የጋራ ሀገር ስላለን ከመንግሥት ጎን በመሆን ሰላምን ማስፈንና ልማትን ማስቀጠል ይጠበቅብናል" ብለዋል።
ሕዝቡ ሰላሙን በመጠበቅ ልማትን ለማፋጠን በሚያከናውናቸው ተግባራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል።
አባ ገዳ አብዮት ድሪባ በበኩላቸው፤ መንግሥት የያዛቸው የሰላምና የልማት እቅዶች እንዲሳኩ ህዝቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ በመምከርና በማስተማር ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ።
መንግስት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሚያደርገው ጥረት ህዝቡ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ አመልክተዋል።