ቀጥታ፡

አዲስ አበባን የሥልጣኔ ተምሳሌት ለማድረግ የ24/7 የሥራ ባህል ማስቀጠል ይገባል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤መስከረም 30/2019(ኢዜአ)፦አዲስ አበባን የሥልጣኔ ማዕከልና ተምሳሌት ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ተቋማት የማስፈጸም አቅማቸውን በማጎልበት የተደመረን የ24/7 የሥራ ባህል ማስቀጠል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2019 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ለሕብረተሰቡ ቃል ከተገባው በላይ በመፈጸምና በድል በማጠናቀቅ፣ በላቀ መልኩ መሥራት የሚያስችል ዳግም ዕድል መገኘቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም ሥራዎችን በላቀ ብቃት ለመፈጸም የሚያስችል የአምስት ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ተዘጋጅቶና ተገምግሞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

የአደረጃጀትና የአመራር ለውጥ መደረጉንና ባለፉት ሦስት ወራት የተተገበረ የ90 ቀን ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱን ያሱሱት ከንቲባዋ፤ በዚህም አስደናቂ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።

የተከናወኑ ተግባራትን ከቁጥር ባሻገር ማየትና ውጤቶችን ከሕብረተሰቡ የኑሮ ጫና ማቃለል እንዲሁም አኗኗርን ከማሻሻል አንጻር መመዘን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ያለንን አቅምና ግብዓቶች በመጠቀም ለተገቢው ሥራ ማዋል ይገባል ያሉት ከንቲባዋ፤ እንደ መንግሥት የኢትዮጵያን የመደመር ስልጣኔ የመገንባት አቅጣጫ እየተከተልን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለመገንባት የተጀመረውን ማላቅና መደመር እንደሚጠይቅ ጠቁመው፤ ለዚህም የተቋማትን የማስፈጸም አቅምና የ24/7 የሥራ ባህልን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

በተቋማት የተናጠል ሥራ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንደማይቻል በመግለጽ፣ ሥራዎችን በጋራና በተናበበ መልኩ መፈጸም አሠራር ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የስልጣኔ ዋና ማዕከል ከተማ በመሆኗ አዲስ አበባ ለዚህ ዓላማ መሳካት ተምሳሌት መሆን እንዳለባትና የምትወዳደረውም ከዘመኑ ከተሞች እንዲሁም ከተቀመጠው ርዕይ አንጻር መሆን እንዳለበት አብራርተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ የግምገማ መድረክ፣ ያለፉት ወራት አፈጻጸምና የቀጣይ 90 ቀናት ተግባራትን ለመፈጸም የሚያስችል አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አመልክተዋል።

አመራሩ ሩጫውን ከቀደመው በማላቅ፣ ውጤት በማስመዝገብና ክፍተቶችን በማረም የተበታተነ አቅምን ደምሮ በትጋት ሊሠራ እንደሚገባም ከንቲባዋ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም