ቀጥታ፡

የህብረ ብሔራዊነት ማህተም

በብዙ ድል ታጅቦ የሚከበረው 19ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

እንደ ዓይን ብሌን በስስት ከሚጠበቁ የሀገር ካስማዎች መካከል ሰንደቅ ዓላማ አንዱና ዋነኛው ነው። አይነኬ የሀገር ምልክትም ነው፤ ሰንደቅ ዓላማ። ለሀገር ምልክት የማይከፈል ዋጋ የለም። የሀገር መከላከያና ሌሎች የጸጥታ አካላት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የደረሰ ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጁለት፤ የሀገር ምልክት የሆኑ አትሌቶችም ደከመኝ ሳይሉ፣ ሳይታክቱና ሕመማቸውን ዋጥ አድርገው በዓለም መድረክ ከፍ እንድትል የሞት ሽረት ትግል የሚያደርጉለት ነው ሰንደቅ ዓላማ። ሁሉም በየመስኩ ደፋ ቀና የሚልለት የሀገር ሰንደቅ ዓላማ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዓሉን አስመልክቶ እንደገለጸው፣ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን የሚከበርበት ዋና ዓላማ ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠት ዜጎች የጋራ እሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት፣ በሀገራዊ አንድነትና በሕብረ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥሩበት ሀገራዊ በዓል ነው።

ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በዋናነት የኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫና አርማ ነው። ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን የጽናታቸው፣ የሕብረታቸው፣ የሕልውናቸውና የሉዓላዊነታቸው ምልክት ነው። ሁለመናቸው ለሆነው ለዚህ ሰንደቅ ዓላማ ጸንቶ መዝለቅ ኢትዮጵያውያን የሚሰስቱት አንዳች ነገር የላቸውም። ታሪክ የሚነግረንም ይህንኑ ሀቅ ነው።

የሀገር ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት፣ የነጻነት፣ የሕዝቦች አንድነትና የክብር ምልክትም ጭምር ነው። ሰንደቅ ዓላማ የትውልዶች ታሪክ፣ የማንነት መገለጫ እንዲሁም የሀገር ሕልውና ምሰሶ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳስታወቀው፣ 19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሐሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ፣ ጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም. በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

ይህ በምክር ቤቱ መሪነት የሚከበረው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በመላ ሀገሪቷ ወቅታዊ ሀገራዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ፣ በድምቀትና በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ ይከበራል።

ዘንድሮ የሚከበረው 19ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በበርካታ ሀገራዊ ድሎችና ውጤቶች የታጀበ ነው። ከእነዚህ ሀገራዊ ድሎች መካከል ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት አጠናቃ አዲሱን የመደመር መንግሥት መመሥረቷ የመጀመሪያው ጉዳይ ሲሆን፣ ሁለተኛው በአሳታፊነትና በአካታችነት ሂደት በስኬት የተጠናቀቀው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ነው።

ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጸንቶ መቆየት በየትውልዱ ዜጎች የሕይወት መስዋዕትነትን ጨምሮ ውድ ዋጋ ከፍለዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይህንን የሉዓላዊነት ምልክት ሳያጎድፉ፣ የሀገርን ዳር ድንበር ሳያስደፍሩና ነጻነትን አስከብረው ለዛሬው ትውልድ አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ቀደምት የሀገር አለኝታዎች የከፈሉት መስዋዕትነት ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ነው። የመከላከያ ሠራዊት ለሰንደቅ ዓላማው ጸንቶ መቆም ሲባል ሕይወቱን፣ ደሙንና አካሉን የገበረ የሀገር አለኝታ ስለመሆኑ ምስክር አያሻም።

ለዚህ ነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀኑን አከባበር ሂደት በተመለከተ ባስታወቀበት መልዕክቱ፣ ይህ በዓል ኢትዮጵያውያን የሀገርን ዳር ድንበርና ክብሯን ለማስጠበቅ ደምና ላባቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያስከበሩትን ሰንደቅ ዓላማ በጋራ የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር የመስጠትና የማክበር ኃላፊነትና ግዴታ አለበት ሲል ያስገነዘበው።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ 18ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተከበረበት ወቅት፣ “የሰንደቅ ዓላማ ቀን ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ፍቅርና አንድነትን የሚያድሱበት፣ የነገ ተስፋቸውን የሚያጸኑበት ነው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አርማ የሉዓላዊነት መገለጫ ማኅተም ነው” ሲሉ መግለጻቸው፣ ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማ እስከ መስዋዕትነት የደረሰ ዝግጁነት ያላቸውን ቀናኢነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ዘንድሮ የሚከበረው 19ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በብዙ ሀገራዊ ድሎችና ተስፋዎች ታጅቦ ነው። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች በርካታ ስኬቶችን ባስመዘገበችበት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ውጤታማ በሆነችበትና የጀመረችውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ባጠናቀቀችበት ወቅት የሚከበር ልዩ ቀን ነው።

በተጨማሪም ሀገራችን በውጭም ሆነ በውስጥ የገጠሟትን ፈተናዎች በዲፕሎማሲያዊ መንገድና በአይበገሬነት መንፈሷ በጽናት እየመከተችና ውጤት እያስመዘገበች ባለችበት፣ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግልጽ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ በስኬት በማካሄድ አዲሱን የመደመር መንግሥት በመሠረተችበት ማግስት የሚከበር መሆኑ ደግሞ እጅግ ልዩ ያደርገዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶቿን “የባንዲራ ፕሮጀክቶች” በማለት ሰይማለች። ለዚህ ምክንያቱ፣ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር መለያ እንደሆነው ሁሉ፣ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም ሀገራዊ ውክልና ያላቸውና የክብር ምልክት በመሆናቸው የሀገሪቱን ታላቅነት፣ ዕድገትና የወደፊት ርዕይ ለዓለም የሚያሳዩ የልማት ውክልናዎች ናቸው። አንድ ሀገር ከነደፈቻቸው ዘመን ተሻጋሪ የልማት ዕቅዶች መካከል ግንባር ቀደም ሆነው የሚተገበሩ፣ ለሌሎች ፕሮጀክቶች አቅጣጫ የሚያሳዩና ስኬታቸው ለሌሎች መንገድ ጠራጊ የሚሆኑትም በመሆናቸው ጭምር ነው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ በጀት፣ ሰፊ ሽፋንና የብዙ ዜጎችን ሕይወት የመቀየር አቅም ያላቸው በመሆናቸው፣ የስኬታማነታቸው ውጤት በጠቅላላው ሀገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ንቅናቄ ይፈጥራል። በባሕር ላይ ዋናዋ መርከብ ትኩረት እንደምትስበው ሁሉ፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን መሪዎች፣ የመገናኛ ብዙኃንንና የሕዝቡን ከፍተኛ ትኩረት የሚስቡና ቅድሚያ የሚሰጠው የሀብት ድልድል የሚደረግላቸው ናቸው። ለዚህም ነው በዜጎችም ሆነ በመንግሥት ልዩ ጥበቃና ክትትል የሚደረግላቸው።

ለአብነት ያህል፣ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች የሀገርን የልማት ቁርጠኝነት፣ አቅምና ርዕይ ለዓለም የሚገልጹ ናቸው። በሀገሪቱ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል በዜጎችም ሆነ በመንግሥት ተሳትፎና ትኩረት የሚስቡ በመሆናቸው “የባንዲራ ፕሮጀክት” ተብለው ይጠራሉ።

የነጻነትና የጸረ-ኮሎኒያሊዝም ምሳሌ

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለዜጎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር የነጻነት ምልክት ነው። ይህ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነጻነትና የጸረ-ኮሎኒያሊዝም ምሳሌ ሆኖ እንዲወሳ ያደረገው የመከላከያ ሠራዊቱና የሕዝቡ የጋራ ተጋድሎ ነው። በዓድዋ ጦርነት ወቅት በዘመናዊ መሣሪያ የተደራጀውን ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት በመመከት፣ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በነጻነት እንዲያውለበልብ የተደረገው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጀግኖች በከፈሉት መስዋዕትነት ጭምር ነው።

ይህ የነጻነትና የጸረ-ኮሎኒያሊዝም ምልክት የሆነው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠብቆ እዚህ ደርሷል፤ ይኸው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ወደፊትም ይቀጥላል። ሀገር በውጭ ወራሪዎች በተፈተነችባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ፣ ሠራዊቱ የሰንደቅ ዓላማዋን ክብር ለማስጠበቅ ግንባሩን ለጥይት መስጠቱን አላቆመም። የሀገርን ድንበር ጥሶ ለመግባት የሚሞክር ወራሪ ኃይልን በመመከት፣ የሉዓላዊነት ምልክት የሆነችውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ለሚያደርግ ሠራዊት ጽናትና ለሀገር ያለውን ጽኑ ፍቅር በግልጽ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለዘለዓለም በነጻነት ከፍ ብላ የምትውለበለበው በጀግኖች የመከላከያ ሠራዊት ውድ ዋጋና መስዋዕትነት ነው። ሠራዊቱ ለሰንደቅ ዓላማው መጽናት የከፈለውና እየከፈለው ያለው መስዋዕትነት የሀገርን ሕልውና የማስቀጠል፣ የሕዝቦችን ሰላም የማረጋገጥና ታሪካዊ ክብሯን የመጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ አደራ ስላለበት ጭምር ነው። ይህንን መስዋዕትነት ማወቅ፣ ማክበርና ለሠራዊቱ የሚገባውን ምስጋና መስጠት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም