በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ መመረቅ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ርዕይ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ መመረቅ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ርዕይ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው
በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ መመረቅ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ርዕይ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት አጋርነት የተቋቋመው ይህ ማጣሪያ ፋብሪካ፤ የማዕድን ዘርፉን ለማጠናከር እና በሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር የተያዘውን ዓላማ ለማሳካት ትልቅ እመርታ ነው።
የማዕድን ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቅድሚያ የሚሰጠው አምራች ዘርፍ ሲሆን፤ በተለይም ወርቅ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። ይህ ተነሳሽነት የሀገሪቱን ሀብቶች ከሀገር ውስጥ ማቀነባበሪያ፣ ከኢንዱስትሪ አቅም እና ዘላቂ እሴት ፈጠራ ጋር ለማስተሳሰር የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን፤ የወርቅ ጥራትን ለመለካት፣ ለማንጠር እና ለውጭ ገበያ ዝግጁ ወደሆኑ ንጹህ ወርቆች ለመቀየር፣ እንዲሁም በተለያዩ የጥራት ደረጃዎች የተሰናዱ የወርቅና የብር ጡቦች ለማምረት ታስቦ የተገነባ ነው።
ማጣሪያ ፋብሪካው በውድ ማዕድናት ማጣራትና ማምረት ረገድ ኢትዮጵያን የቀጣናው ማዕከል ለማድረግ መሠረት የሚጥል ሲሆን፤ የወርቅ ዋጋ አተማመን ላይ ግልጽነትን፣ የጥራት ማረጋገጫን እና እምነትን ያሳድጋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ላቀ የሀገር ውስጥ እሴት፣ ጠንካራ የኢንዱስትሪ አቅም እንዲሁም በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ ገበያዎች ሰፊ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚረዳ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።
ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ግልጽ የሆነ ትልቅ ርዕይ ያነገበ ነው፤ ይህም ጥሬ ማዕድናትን ዝም ብሎ ከመቆፈር ባለፈ፣ ማቀነባበር፣ ማምረት እና በሀገር ውስጥ የላቀ እሴት መፍጠር ላይ የሚያተኩር ነው።