የሀገርን ልማት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ በንቃት መሳተፍ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ልማት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ በንቃት መሳተፍ አለበት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠንና ሰላምን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት ሁላችንም በተሰማራንበት የሙያ መስክ በንቃት መሳተፍ ይገባናል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
ሰባተኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
በምክር ቤቶቹ የጋራ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላምና ተረጋግቶ የመኖርን ዋጋ በጥልቅ የሚያውቅ፣ የጦርነትን አጉዳይነት በጉልህ የሚረዳና የሚጠየፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የታላቅ ሀገርና የነባር ስልጣኔ ባለቤት የሆነ ህዝብ መገለጫ ሀገርን ማጽናት፣ ሉዓላዊነትን ማስከበርና ሰላምን መጠበቅ በመሆኑ የተጀመሩት የልማት ጉዞዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በስራና በትጋት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የመንግስት ተግባር ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ የጋራ ሀላፊነት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንኑ ጥረት ጠብቆ የማቆየት፣ የማስቀጠል እና የማሻሻል የጋራ ሀላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በማንሳት የሚታዩ ተጨባጭ ለውጦች ለሀገር እድገት መሠረት እየጣሉ ናቸው።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ጉደታ ደንደነ፤ የልማት ሥራዎቹ ተጨባጭ ለውጦችን አሳይተዋል። በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶች አዲስ አበባ በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗንም ነው የሚያንጸባርቁት።
የቢሸፍቱ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያን ጨምሮ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሁሉም ዜጋ ከመንግሥት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አድማሱ ዱላ መንግሥት በልማት ሥራዎች ላይ ውጤታማ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሕብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመተባበር መትጋት እንዳለበት ተናግረዋል።
ለሀገር ዕድገት ልጆችን ከማስተማርና ከመምከር ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ራሔል መንገሻ ናቸው።
ለተጀመሩ የልማት ሥራዎች መሳካት ከከተማ አስተዳደሩና ከመንግሥት ጎን በመቆም በጋራ መሥራት እንደሚገባም አብራርተዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ጥላሁን ዋቅጅራ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በልማት ጉዞ ላይ ትገኛለች። በተለይም ቀደም ሲል በወንዝ ዳርቻ የልማት እጥረት የነበረባቸው አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት መልካቸውን ቀይረው መታየታቸው አበረታች ነው።
ወይዘሮ ዛህራ ኑረዲን፤ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ በሚገኘው ልማት ላይ እያንዳንዱ ዜጋ ባለው አቅም መሳተፍ እንደሚጠበቅበት ጠቁመው፤ ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች መፋጠን የጎላ ሚና ሊጫወት እንደሚገባ ተናግረዋል።