ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ የጋራ ትብብር እና ልማት መሰረት ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ የጋራ ትብብር እና ልማት ቁልፍ ሚና የሚጫወት ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ገለጹ።

አምባሳደር ዘሪሁን ከኢዜአ ባደረጉት ቆይታ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚከሰቱ እንደ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ እና ድርቅ ያሉ ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተደራራቢ ፈተናዎች ለመቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ለትብብር፣ለቀጣናዊ ትስስር እንዲሁም ለዓባይ ውሃ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት የማይናወጥ አቋም እንዳላት ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ትስስር መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ስትገነባ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተር ጄነራሉ፤ለቀጣናዊ ልማት፣የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ለመገንባትና የኢነርጂ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

ግድቡ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የተከናወነ ትልቅ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ነው ያሉት አምባሳደሩ የአየር ንብረት ፈተናዎችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችሉ ሰፊ ዕድሎችን ይዞ መምጣቱን አመልክተዋል።

ግድቡ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ በውሃ ማከማቸት እና የጎርፍ አደጋን በመቀነስ ረገድ ለሱዳንና ለግብጽ የተሻለ ጥቅም እንደሚያስገኝ ነው ያብራሩት።

አምባሳደሩ አክለውም የህዳሴው ግድብ ውሃ የሚገኝበት አካባቢ ከግብጹ አስዋን ግድብ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ትነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው ይህም በትነት ምክንያት የሚባክነውን የውሃ መጠን በእጅጉ እንደሚቀንስ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ግድቡ የውሃ ፍሰትን በሚገባ በመቆጣጠር ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ፣በታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት በንብረት፣ በሰው ህይወት እና በዜጎች መኖሪያ ላይ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋና ውድመት መከላከል እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ድርቅን የመቋቋም ሂደትን በተመለከተ በህዳሴው ግድብ የሚከማቸው ውሃ በረጅም የድርቅ እና የውሃ እጥረት ወቅት በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የተሻለ ትብብር እንደሚፈጥር እና የውሃ ዋስትናን እንደሚያረጋግጥ አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ግድቡ የቀጣናው ስትራቴጂካዊ ሀብት እንደሆነ ገልጸው የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል የጎረቤት ሀገራትን የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።

ወደ ንጹህ የኃይል ምንጮች የሚደረገውን ሽግግር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚደግፍም ገልጸዋል።

የታዳሽ ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ማስፋት የድንበር ተሻጋሪ የኢነርጂ ትብብርን እንደሚያጠናክርና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገውን ሰፊ ጥረት እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

አምባሳደር ዘሪሁን የህዳሴውን ግድብ ዘላቂ ጥቅሞች ለማረጋገጥ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በጋራ የውሃ ሀብት ላይ የሚደረግ ትብብር ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር እንዲሁም የጋራ የልማትና አካባቢያዊ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ እንደሆነም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም