ቀጥታ፡

‎በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር አቅም ያለው ፋብሪካ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ)፦ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር አቅም ያለው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ፋብሪካ ሥራ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባውን ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ሥራ መጀመሩን ሳበስር በታላቅ ደስታ ነው ብለዋል።


 

‎የማጣሪያ ፋብሪካው በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር አቅም ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።

ፋብሪካው፤ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር፣ የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ ለማጠናከር እና ሀገራችንን በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ረገድ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።


 

‎ይህ ውጥን፤ ሀብቶቻችንን ከኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማስተሳሰር ወጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ይበልጥ ግልጽ እና ተወዳዳሪ የሆነ የወርቅ እሴት ሰንሰለት ለመገንባት የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም