የሴቶች አካታችነት ምኅዳር መስፋት፤ ኢትዮጵያን የመገንባት ፍኖት - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች አካታችነት ምኅዳር መስፋት፤ ኢትዮጵያን የመገንባት ፍኖት
በየጸዳወርቅ ታደለ
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ርህራሔ፣ ጥንካሬ፣ ሕይወት፣ ፍቅርና ውበት የሀገርና ሴት መገለጫዎች ናቸው። በቋንቋ፣ በስያሜ፣ በታሪክና በተግባር ሲታዩ ሀገር እና ሴት አንድ የሚያደርጋቸውን ተመሳስሎሽ ያሳያሉ። ሴት የሕይወት መሠረት፣ የቤት ማዕዘንና የትውልድ አርበኛ ናት። ሴት ልጅ የተቸራት ሁለገብ ሙያ፣ ዕውቀት፣ ብልሃትና ብቃት የሀገር ግንባታ ድርሻዋን ጉልህ ያደርገዋል።
ሀገር ስትጠራም በእናት ትመሰላለች። ይህ ስያሜ አባባል ብቻ አይደለም። የእናትነትን ታላቅ ባሕርይ ለሀገር የመስጠት ጥልቅ ፍቅር ነው። አንዲት ሴት ልጅን በእቅፏ እንደምታሳድግ ሁሉ፣ ሀገርም ዜጎቿን አስጠልላ የምታሳድግ ግዙፍ ጥላ ናት። ለዚህም ነው ሁለቱም የመጠለያና የደህንነት ተምሳሌቶች ናቸው የሚባሉት።
ይህ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ሴቶች በተሰማሩበት መስክ ስኬታማነታቸው የላቀ እንደሚሆኑ ያሳያል። ሴቶች ከቤታቸው አልፈው በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ እርስ በርስ በመረዳዳት፣ በባህላዊ እሴቶችና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ሚና በመወጣት የሕብረተሰብ መስተጋብር ገመድ ናቸው። በኢኮኖሚ መስክም ለሀገር የልማት መርሃ ግብሮች ስኬት ከፍተኛ ዐሻራ አላቸው።
የኢትዮጵያ ሴቶችም የርኅራሔ፣ የአብሮነት መሠረትና የትውልድ ግንባታ ተምሳሌት ናቸው። ጀግንነትም የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ነጻነት በማስከበር ሂደት በተግባር ተፈትሎ የሚያልፍበት መገለጫቸው ነው። ለዚህም ከዓድዋ ድል የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ እስከ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ዐሻራቸው ሕያው ነው።
ዛሬም የመደመር መንግሥት ሴቶችን በከፍተኛ የመንግሥት አመራርና በውሳኔ ሰጪነት በማሳተፍ፣ ያላቸውን ብቃትና አቅም ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ለውጥ በማዋል የሴቶችን ሚና የበለጠ የሚያጎለብት ምኅዳር ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ የወለደው የመደመር መንግሥት፣ ሴቶች ብቃታቸውን፣ ክህሎታቸውንና ተሰጧቸውን ለሀገር ግንባታ የሚያውሉበትን አስቻይ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምኅዳር ፈጥሯል። የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማጎልበት አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል። ይህም በትምህርት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በተቋም ግንባታና በውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ ሴቶች የማድረግ አቅማቸውን ማስመስከር ያስቻሉ ተግባራዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ አድርጓል።
በተለይም የመደመር መንግሥት የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ለማጎልበት የፈጠረው ልምምድ አሳታፊና አካታች ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቁልፍ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አጀንዳነት የተያዘ ነው። እነዚህና መሰል ተግባራትም የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ኢትዮጵያ አካታችና አሳታፊ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ምኅዳር እየፈጠረች መሆኗን ያመላክታሉ።
የመደመር መንግሥት በፌዴራል፣ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች የካቢኔ አወቃቀር ለሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ድርሻ መስጠቱ ሁለገብ ሙያዊ ክህሎታቸውን ለሀገር ግንባታ እንዲያውሉ እያስቻለ ይገኛል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰይሟል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅራቢነት በተዋቀረው አዲሱ ካቢኔ ውስጥ ከ22 የመደመር መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ውስጥ 9 ሴቶች ሹመት አግኝተዋል። ይህም ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካትና የሕዝብ አደራ በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አካታች ሥርዓት የመገንባት መሰረት ነው።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመደመር መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካቀረቧቸው 22 ዕጩዎች ሚኒስትሮች መካከል ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የገንዘብ ሚኒስትር፣ ሃና አርአያሥላሴ የፍትሕ ሚኒስትር፣ ያስሚን ወሃብረቢ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር፣ ዶክተር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስትር፣ ዓይናለም ንጉሴ የገቢዎች ሚኒስትር እና ሰላማዊት ካሳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በማድረግ ሹመት ሰጥቷል።
እንዲሁም ዓለምጸሃይ ጳውሎስ የማዕድን ሚኒስትር፣ ሻዊት ሻንካ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ፍሬሕይወት ታምሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሲያደርጉ ሹመቱን ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ሚኒስትሮቹም ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ ሕዝባዊ አደራና ኃላፊነት ተረክበዋል። ይህም ሴቶችን ከማሳተፍ በላይ የተሻገረ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም የመደመር መንግሥት አሳታፊና አካታችነት የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ማጠናከሩን የሚያሳይና እጅግ የሚያኮራ ውሳኔ መሆኑን አንስተዋል። በካቢኔ አወቃቀር ውስጥ በርካታ ሴቶች መካተታቸው ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሀገራት ጭምር ተምሳሌት መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያ በፓርላማ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በከንቲባነት ጭምር ሴቶችን በቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመሾም አህጉራዊና ዓለም አቀፍ አርዓያነቷን ማሳየቷንም አስታውሰዋል። በቀጣይም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማጠናከር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የሴቶችን የመፈጸም አቅምና ብቃት ለማረጋገጥ ብሎም ተጨማሪ ዕድል ለመስጠት የመደመር መንግሥት ዝግጁ ነው። የመደመር መንግሥት አካታች የዲሞክራሲ ሥርዓትን መገንባት ብቻ ሳይሆን እውን ማድረግ እንደቻለ ምስክር የሚሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ።
ሴቶችን በማብቃት፣ በማካተትና ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ የተወሰዱ ትልልቅ ውሳኔዎችና ስኬታማ ሥራዎች በመደመር መንግሥት የተጀመሩ ዛሬም ወደፊትም የሚቀጥሉ ናቸው። ሴቶች የበለጸገች ኢትዮጵያን በመቅረጽ ሂደት ውስጥ ያላቸው አበርክቶ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በእርግጥም ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ ለሰነቀችው ኢትዮጵያ የሁሉንም ዜጎች አቅም፣ ዕውቀትና ተሰጥኦ ለሀገር ግንባታ ማሰለፍ ማለት ነው። ከዓድዋ ድል የነፃነት ተጋድሎ እስከ ዛሬው የልማትና የለውጥ ጉዞ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ያስመዘገቡት ጀግንነትና ሁለገብ ብቃት ለዚህ ታላቅ ርዕይ ወሳኝ መሰረት ነው። የመደመር መንግሥት ሴቶችን በከፍተኛ አመራርና ውሳኔ ሰጪነት በማሳተፍ የጀመረው እመርታም ይህንኑ አቅም ወደ ሀገራዊ ውጤት ለመቀየር የሚያስችል አካታች ምኅዳር ፈጥሯል። ስለሆነም ሴቶች በእኩልነት፣ በብቃትና በኃላፊነት የሚሳተፉባት፣ የሁሉንም ዜጎቿን አቅም የምታሰልፍና የጋራ ብልፅግናን የምታረጋግጥ ኢትዮጵያን መገንባት የዘመኑ ታሪካዊ ዐሻራ ነው። ትልቅ ሀገር የምትገነባው በትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይዋንም ወደ እውነት የምትቀይረው የሁሉንም ዜጎች አቅም በማካተት ነው።