ቀጥታ፡

የመደመር መንግስት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት የበኩላችንን እንወጣለን

ሆሳዕና፤ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ)፡- የመደመር መንግስት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች መንግስት ባለፉት ዓመታት በከተማና በገጠር ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን አንስተዋል።

ከነዋሪዎች መካከል አቶ አዳነ ሴዲሶ እንዳሉት፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት በየአካባቢው ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በተለይ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበባቸው እንደሆኑ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

አዲስ የተመሰረተው የመደመር መንግስት በተለያየ ዘርፍ የተጀመሩ ልማቶችን ከማጠናከር ባለፈ ለልማት እንቅፋት የሆነውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ለመከላከል የተለየ ትኩረት መስጠቱ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።  

በቀጣይም ሙስናን በመከላከል የህዝብን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ሥራዎች ሙሰኞችን ከማጋለጥ ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።


 

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ዲያና አዳነ ናት።

በዚህም የዜጎች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ጠቁማ፣ የአምስት ሚሊዮን የኢትዮ-ኮደርስ ኢንሼቲቭ ትግበራ በተለይ ወጣቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀታቸው ተወዳዳሪና ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግራለች፡፡

አዲስ የተመሰረተው የመደመር መንግስትም በዲጂታል ዘርፍ እንደሀገር የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የያዘውን ግብ ለማሳካት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ተናግራለች።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን ተግባራዊ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ምህረት ኦሳሞ ናቸው፡፡


 

ዲጂታል አሰራሩ አገልግሎት ለማግኘት ይስተዋል የነበረውን እንግልትና ለብልሹ አሰራር የነበረን ተጋላጭነት ማስቀረቱን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ መጠናከር አለበት ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም