አርሰናል ከሊድስ ዩናይትድ እና ማንችስተር ዩናይትድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ: የዕለቱ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ከሊድስ ዩናይትድ እና ማንችስተር ዩናይትድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ: የዕለቱ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ)፦ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክንያት ለሶስት ሳምንት ተቋርጦ የነበረው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በስድስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይመለሳል።
በዕለቱ ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ላይ አርሰናል ሊድስ ዩናይትድን በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።
የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል በ12 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሊድስ ዩናይትድ በበኩሉ በዘጠኝ ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
መድፈኞቹ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቡድኑ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ማንችስተር ሲቲ ጋር በነጥብ እኩል ይሆናል።
በሊጉ መልካም ጅማሮ ያደረገው ሊድስ ዩናይትድ በአምስተኛ ሳምንት ከክሪስታል ፓላስ ጋር ያለ ግብ አቻ መለያየቱ የሚታወስ ነው።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በኦልትራፎርድ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባለሜዳው ማንችስተር ዩናይትድ በአምስት ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም።
በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።
ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች እጅጉን ወሳኝ ነው።
ዩናይትድ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ስፐርስ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ በሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፍልሚያ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ቼልሲ ከቦርንማውዝ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል።
ቼልሲ በሰባት ነጥብ 10ኛ ደረጃን ሲይዝ ቦርንማውዝ በሶስት ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል። ቦርንማውዝ እስከ አሁን በሊጉ ምንም ጨዋታ አላሸነፈም።
ቼልሲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና ቦርንማውዝ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ይፋለማሉ።
ሰንደርላንድ ከብራይተን ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በስታዲየም ኦፍ ላይት ይጫወታሉ።
ባለሜዳው ሰንደርላንድ በአራት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ብራይተን በ10 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ሰንደርላንድ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል። ተጋጣሚው ብራይተን በበኩሉ በአምስተኛ ሳምንት የወቅቱን የሊጉን ሻምፒዮን አርሰናል 3 ለ 0 ረትቷል።
አስቶንቪላ ከብሬንትፎርድ እና ኤፕስዊች ታውን ከፉልሃም በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።