በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና ማስከበር ረገድ ጉልህ አዎንታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና ማስከበር ረገድ ጉልህ አዎንታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ) ፦በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና ማስከበር ረገድ የሰላምና የእርቅ ጥረቶች፣ የፍትሕ ሥርዓቱ መሻሻሎችና የተጋላጭ ማኅበረሰቦችን መብት ለማስጠበቅ በተወሰዱ እርምጃዎች ጉልህ አዎንታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ኮሚሽኑ ከሰኔ 2017 እስከ ሰኔ 2018 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍነውን አምስተኛ ዓመታዊ ሪፖርቱን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ በመግለጫቸው፤ በእስር ላይ ከነበሩ ሰዎች መካከል ከ729 በላይ የሕግ ታራሚዎች የይቅርታ አሠራር ሂደቶችን ተከትለው በይቅርታ፣ በቅድመ-ሁኔታ ክስ በማቋረጥ እንዲሁም በሌሎች የሕግ ሂደቶች ተፈተዋል።
በተለይም የፍትሕ አካላት እና ፍርድ ቤቶች በቅንጅት በመሥራት፣ የታሰሩ ሰዎችን በይቅርታ፣ በዋስትናና በነጻ የሕግ ድጋፍ ከእስር እንዲለቀቁ ማድረጋቸው እንደ መልካም ተሞክሮ የሚወሰድ መሆኑ በሪፖርቱ መካተቱን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በ2018 በጀት ዓመት 98 ማረሚያ ቤቶች፣ 649 ፖሊስ ጣቢያዎችና 10 መደበኛ ያልሆኑ የማቆያ ስፍራዎች መጎብኘታቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በዚህም በበርካታ ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎች መከናወናቸው በበጎ ጎን መነሳቱን አብራርተዋል።
የአእምሮ ጤና ሕክምና አገልግሎቶች በሪፈራል ሆስፒታሎች መስፋፋታቸውና በጤና መድን ሽፋን ውስጥ መካተታቸው አዎንታዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ የሕፃናት ማቆያና ተሐድሶ ማዕከል የታዩ መሻሻሎች መኖራቸውን አብራርተዋል።
የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ፖሊሲ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አካታችነትን የሚያጎላ አቅጣጫ መከተሉና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች በአዎንታዊነት መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
ለአደጋ ሥጋት ምላሽ የሚሰጥ ፈንድ የሚያቋቁም ደንብ መጽደቁ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በትብብር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ስትራቴጂዎች መቀረጻቸውና የዲጂታል መታወቂያ ለተፈናቃዮች ተደራሽ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩልም የስደተኛ ማኅበራት እንዲቋቋሙ መፈቀዱ፣ ስደተኞችን ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ለማቀላቀል የሚያግዙ የሕግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውና የተሻሻለው የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅ መጽደቁ በሪፖርቱ መካተቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተሻሻለው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ የሴቶችን፣ የወጣቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሁም ቅሬታዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመፍታት የሚያስችል ምቹ የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋቱ በክትትል የታዩ አዎንታዊ ለውጦች መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ወደ መጨረሻው የምክክር ምዕራፍ በመሸጋገር ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄዱና አጀንዳዎችን ማስረከቡ፣ እንዲሁም መንግሥት የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት መግለጹ በበጎ ጎን ተነስተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሕግ የተሰጠውን ተልዕኮ በነጻነትና በገለልተኝነት በመወጣት፣ ሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም የሚከበሩበት፣ የሚጠበቁበትና የሚሟሉበት ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ኢሰመኮ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችንና የተፈናቃዮችን መብት የሚያስጠብቁ ሕጎች እንዲጸድቁ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረቡን አስታውሰው፤ በሪፖርቱ የተነሱ ጉዳዮች የሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚያስፈልግ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ አመልክተዋል።