በደቡብ ኦሞ ዞን በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ450 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኦሞ ዞን በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ450 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል
ጂንካ፤ መስከረም 29/2019(ኢዜአ)፡-በደቡብ ኦሞ ዞን በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ450 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን የዞኑ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በዞኑ በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት ዛሬ በዲመካ ከተማ እውቅና ተሰጥቷል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ እንዳሉት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በርስ የመረዳዳት ባህልን እያሳደገ መጥቷል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የአንድ ሰሞን ርብርብ ብቻ ሳይሆን በተቋማዊ አሰራር እና ዕቅድ ተካቶ ሁልጊዜ የሚተገበር መሆን እንዳለበት አንስተዋል።
በዞኑ በጎ ፍቃደኞች በክረምት ወራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነው፤ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የተጀመሩ በጎ ሥራዎችን ዘላቂ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤልያስ ሰዕሲ፤ የ2018 የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በ20 የትኩረት መስኮች ሲከናወን መቆየቱን አንስተዋል።
በልማት ሥራዎቹም ከ143 ሺህ በላይ ወጣቶችን እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በልማት ስራዎቹ ከ450 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም ከመንግሥት ሊወጣ የነበረን ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል ብለዋል።
የአረጋውያን ቤት እድሳት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የደም ልገሳ፣ የአካባቢ ፅዳት፣ ለአቅመ ደካሞች ማዕድ ማጋራት እና ሌሎችም ተግባራት ከተከናወኑት የልማት ሥራዎች መካከል በዋናነት እንደሚጠቀሱም ገልጸዋል።
በበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ የተሳተፉት ወጣት ስጦታው አመዴ እና ራሔል ታደሰ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለህሊና እርካታ የሚሰጥና በፈጣሪ ዘንድም ዋጋ ያለው አበርክቶ መሆኑን ተናግራለች።
በክረምት ወራት ወጣቶች የአረጋውያንን ቤት በማደስ፣ ደም በመለገስ እና በተራቆቱ አካባቢዎች ችግኝ በመትከል ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ በዚህም ደስተኛ መሆናን ገልጻለች።
በዞኑ የተሰጠው ዕውቀትና ሽልማትም ተግባሩን በበጋ ወራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ መነሳሳት እንደፈጠረላቸውም ተናግራለች።፡
በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች እንዲሁም ተቋማት ዕውቅና ሽልማት ተሰጥቷል።