ቀጥታ፡

የሕንድና አፍሪካ የረጅም ዘመን ትብብር በሕንድ ቪክሲት 2047 ርዕይና በአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29 /2019 (ኢዜአ)፦ የሕንድና አፍሪካ የረጅም ዘመን ትብብር በሕንድ ቪክሲት 2047 ርዕይና በአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር (ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በሕንድ-አፍሪካ ትብብር ላይ ያተኮረ መድረክ በዓድዋ ድል መታሰቢያ አዘጋጅቷል።


 

በመድረኩ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር መሀመድ ኢድሪስን ጨምሮ አምባሳደሮችና የዘርፉ ምሁራን የተገኙ ሲሆን የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር (ዶ/ር) ንግግር አድርገዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ በታሪካዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በመገኘታቸው ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ የድል ታሪክ ብቻ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነትና የአሸናፊነት ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።

ዓድዋ ለሰብዓዊ ክብር መዋደቅ፣ ለሉዓላዊነት መታገል፣ ለፖለቲካ ነፃነት መሟገት በራስ አቅም የመወሰን ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።

ሕንድና አፍሪካ በቅኝ ገዥዎች አማካኝነት ሰብዓዊ ኪሳራ እንደደረሰባቸው፣ ሀብታቸው እንደተመዘበረባቸው ገልጸው፤ በመካከላቸው የሕንድ ውቅያኖስ የማይጋርደው ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት አላቸው ብለዋል።

የሕንድ ውቅያኖስ ውኃ ብቻ ሳይሆን የሕንድና አፍሪካ የሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ማሳለጫ የፍጥነት መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕንድና አፍሪካ በሙዚቃ፣ በባህል፣ በአስተሳሰብና በአገር በሕንድ ውቅያኖስ የተሳሰሩ ናቸው ብለዋል።

በመካከላቸው ያለው የነፃነት ታሪክ የተሳሰረ መሆኑን በማንሳት፤ በተቋማት ግንባታና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የዓለም ነባራዊ ሁኔታ መቀየሩን ገልጸው፤ ትብብራቸውም በደቡባዊ ዓለም ማዕቀፍ በዚያው ልክ ማደግ አለበት ብለዋል።


 

የሕንድ ቪክሲት (VikSit Bharat) 2047 ርዕይ ከአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ጋር ጎን ለጎን የሚሄድ ሳይሆን ተጣጥሞ የሚመራ ትልቅ ግብ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአፍሪካና የሕንድ የንግድ ግንኙነት መገደብ የለብንም፤ በመሠረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቴሌኮም እና በመሰል ዘርፎች ያለውን ትብብር ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያና በሕንድ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ደግሞ በአክሱማዊት ሥልጣኔና በአዱሊስ ወደብ ንግድ የሚመነጭ የረጅም ጊዜ ትብብር መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያና በሕንድ መካከል ያሉት የትምህርትና ሥልጠና ግንኙነት ከመደበኛ ዲፕሎማሲ የተሻገረ መሆኑን ገልጸው፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሙዲ መሪነት የሁለቱ ሀገራት የግንኙነት ሽግግር በፍጥነት እየተጓዘ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ 600 በላይ የሕንድ ኩባንያዎች በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸው፤ ከ75 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር በኢነርጂ፣ በግብርና፣ በሕክምና መገልገያና መድኃኒት፣ እንዲሁም በስኳር ፕሮጀክት በጋራ እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕንድና ኢትዮጵያ በብሪክስ እና በአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም