ቀጥታ፡

ሀገራዊ ቀጣይ የልማት ግቦችን ለማሳካት ሁሉም ዜጋ በተደመረ አቅምና ትብብር መስራት አለበት-ምሁራን

ጋምቤላ፤ መስከረም 29/ 2019 (ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ቀጣይ የልማት ግቦችን ለማሳካት ሁሉም ዜጋ በተደመረ አቅምና በትብብር ሊሰራ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግስት ምስረታ ዳግም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲሰየሙ በሚቀጥሉት ዓመታት መንግስት ለመተግበር ያቀዳቸውን ዋና ዋና የልማት ግቦች ይፋ አድርገዋል።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንም ሀገርን ወደ ተሻለ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መዋቅራዊ ሽግግር የሚያደርሱ እነዚህን የልማት ግብች ለማሳካት ዜጎች በተደመረ አቅምና ትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የታዩ የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል የሀገሪቱን እድገትና ብልጽግና ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግርም ተናግረዋል።

ከዩኒቨርሲቲው ምሁራን መካከል ጀምበሩ ዓለሙ (ዶ/ር) እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ያደረጓቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት አቅጣጫዎች በተደመረ አቅምና በትብብር እውን ማድረግ ይገባናል ብለዋል።

በተለይም በምግብ ዋስትና፣ በመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በመሰረተ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች የታለሙትን የልማት ግቦች ዳር ለማድረስ የሁሉም ዜጋ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

በመደመር መንግስት የተያዙ የልማት ግቦች ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን የሚያጠናክሩና ለሀገሪቱ ህዝቦች ትልቅ ተስፋን የሚሰጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

እንደሀገር በቀጣይ ለማከናወን የተያዙ የልማት ግቦችን ውጤታማ ለማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ ክህሎት የተላበሰ ማህበረሰብ መገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

መንግስትም የህዝብን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ህዝቡ በተደመረ አቅም ልማት ላይ እንዲረባረብ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉም ምሁሩ ገልጸዋል።


 

ሌላው የዩኒቨርሲቲ ምሁር ጌታቸው በቀለ (ዶ/ር) እንዳሉት በቀጣይ ዓመታት ሊተገበሩ የታቀዱት የልማት ግቦች ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ ልማትን የሚያረጋግጡ ናቸው።

የልማት ዕቅዶቹ በተለይም ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ የአርንጓዴ አሻራ፣ የመንገድ፣ የኢነርጂና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ይበልጥ የሚያጎለብቱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በመሆኑም በመንግስት የተያዙ የልማት ዕቅዶችን ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም ዜጋ በትብብርና በአንድነት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለዕቅዱ መሳካት የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩም ጌታቸው (ዶ/ር) አክለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም