የኢትዮጵያ እና ህንድ ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ፡ ከዘመናት ታሪካዊ ቁርኝት ወደ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ህንድ ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ፡ ከዘመናት ታሪካዊ ቁርኝት ወደ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት
የኢትዮጵያ እና የህንድ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀ ጥልቅ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበራዊ መሠረት ያለው ነው።
ግንኙነቱ የተጀመረው በአክሱም ስልጣኔ ዘመን በጥንታዊቷ የአዱሊስ ወደብ በኩል በነበረ የባህር ላይ የንግድ ልውውጥ ነው።
የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነት መገለጫ ነው።
ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ በ1948 በይፋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱ ሲሆን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ በመሆን በኒው ዴልሂ ኤምባሲዋን ከፍታለች።
በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም በርካታ የህንድ መምህራን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ላይ ታሪካዊ አሻራ ጥለዋል።
ይህ የዘመናት ወዳጅነት የሕዝቦችን ትስስር በማጥበቅ ለዛሬው ዘመናዊና ዘርፈ-ብዙ ትብብር ጠንካራ መነሻ ሆኗል።
ይህ ታሪካዊ መሠረት በሀገራቱ መሪዎች ተከታታይ የጉብኝት ልውውጦች ይበልጥ እየጎለበተ መጥቷል።
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያደገ የመጣው የሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እ.አ.አ በሴፕቴምበር 2026 በ18ኛውን የብሪክስ (BRICS) መሪዎች ጉባኤ ለመታደም ወደ ህንድ ያቀኑ ሲሆን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በሌላ በኩል፣ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እ.አ.አ ዲሴምበር 2025 በአዲስ አበባ ያደረጉት ታሪካዊ ይፋዊ ጉብኝት ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በይፋ አድጓል።
በዚህ ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ ውስጥ ንግድ፣ መከላከያ፣ ቴክኖሎጂ እና ሰው ኃይል ልማት ከሀገራቱ የትብብር መስኮች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ህንድ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ650 በላይ ኩባንያዎች ያሏት ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) ፍሰት ቀዳሚ ስፍራ ከያዙ ሀገራት ተርታ አሰልፏታል።
ይህንን ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ለማቀናጀት የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን እንደ ተቋማዊ ማዕቀፍ እያገለገለ ይገኛል።
ትላንት ማታ አዲስ አበባ የመጡት የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራማኒያም ጃይ ሻንካር (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው ይፋዊ የስራ ጉብኝት የሀገራቱ ጥብቅ ወዳጅነት ማሳያ ነው።
ሱብራማኒያም ጃይ ሻንካር (ዶ/ር) ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በሁለትዮሽ እና በወቅታዊ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በውይይታቸውም በትምህርት፣ በባህል፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በዲጂታላይዜሽን ዘርፎች ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማስፋፋትና ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የህንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ በኒው ዴልሂ በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ላደረገችው ውጤታማ ተሳትፎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሁለቱ ሀገራት የብሪክስ አባል መሆን የሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ትብብራቸውን የበለጠ አጠናክሮታል።
ሀገራቱ በጥምረቱ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራትና የደቡባዊ ንፍቀ ዓለም (Global South) ድምጽ በመሆን እየሰሩ ይገኛል።
ይህም የሀገራቱ የጋራ የልማት ጥቅሞች እንዲከበሩ የሚያስችል የባለብዙ-ወገን ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል ምሰሶ ነው።
የኢትዮጵያ እና የህንድ ግንኙነት ከጥንታዊ የአዱሊስ የባህር ላይ ንግድ ተነስቶ ዛሬ ላይ ወደ ላቀ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተሸጋግሯል።
መጻኢ የትብብር ጊዜም በስትራቴጂካዊ አጋርነት እና በጋራ ዕድገት ላይ ተመስርቶ የበለጠ ፍሬያማ እንደሚሆን ይታመናል።