ቀጥታ፡

ለህዝብ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት በትብብር  እንሰራለን-ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 

አዳማ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ)፡- ለሀገር ግንባታ እንዲሁም ለህዝብ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት በትብብር እንደሚሰሩ ተፎካካሪ  የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን  አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡ 

በዚህም ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ለሁለተኛ ጊዜ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሰየሙን ተከትሎ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር እንዲሁም የመንግስት  የቀጣይ አቅጣጫ መነሻ በማድረግ ኢዜአ በአዳማ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር በየነ ደሳለኝ  እንዳሉት ሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ፍትሀዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ የተሳተፈበት ነው።

በምርጫው ብልጽግና ፓርቲ በማሸነፉ አዲስ መንግስት መመስረቱን  ጠቁመው ይህንኑ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልእክትና የመንግሥት አቅጣጫ በሳልና ለህዝብ የሚበጅ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።

በተለይም መንግስት በቀጣዮቹ አመታት ለማከናወን የያዛቸው እቅዶች  ባለፉት አመታት በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት፣ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል አገልግሎት፣በገጠርና በከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ይበልጥ ለማስፋፋትና ለማሳለጥ ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት ለታጠቁ ሃይሎች ያቀረበው የሰላም ጥሪም ፓርቲያቸው እንደሚደግፈው ገልጸው ሁሉም ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በመሆኑም  አዲስ የተመሰረተው መንግስት የቀየሳቸው የሙስና መከላከል፣ የባህር በር አጀንዳ፣ ሁሉን አቀፍ ልማትና ሌሎችም  እቅዶች እንዲሳኩ እና  ለህዝብ ዘላቂ ሰላም እና ተጠቃሚነት ፓርቲያቸው  በጋራና በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

መንግስት ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጎሪጥ ከመተያየት ይልቅ በጋራ መስራት ሀገር ያሻግራል ብሎ  ቁርጠኝነቱን ማሳየቱ ለሀገራችን ህዝቦች ዋስትና ነው ሲሉም  አክለዋል።


 

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የማእከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሀብታሙ ተሰማ በበኩላቸው አዲስ የተመሰረተው  መንግስት የያዛቸው ውጥኖች ተግባራዊ ከሆኑ ዘርፈ ብዙ ለውጥ ይመጣል ብለን እናምናለን ብለዋል።

አዲሱ የመንግሥት ምስረታ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠልና ኢትዮጵያን ለማሸጋገር የሚያስችል ዕድል በመሆኑ በትብብር ልንሰራ ያስፈልጋል ብለዋል።

 በጨካ ያሉ የታጠቁ ሃይሎች መንግሥት ያቀረበላቸውን እድል በመቀበል በሀገረ መንግስት ግንባታ የራሳቸውን አሻራ ሊያኖሩ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

 መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ፍላጎት ማሳየቱ የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸው ይህም በሃገሪቱ አንጻራዊ የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱን ያሳያል ብለዋል።

 ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።


 

 የአዲስ ትውልድ ፓርቲ አባል ወጣት ቦንቱ አብርሃም በበኩሏ መንግስት ባለፉት ዓመታት  በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ዘርፍ ያስመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠል በሙስና መከላከል ላይ አተኩሮ ሊሰራ ያስፈልጋል ብላለች።

 መንግስት የተያዙ የልማት ውጥኖች በሙስና እንዳይደናቀፉ ምንጩን ለማድረቅ የያዘው አቅጣጫ የሚደገፍ መሆኑን ጠቁማ እቅዱ እንዲሳካ ሁሉም ዜጋ ሊተባበር እንደሚገባ አመልክታለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም