ቀጥታ፡

በክልሉ የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽና ፍትሐዊ ለማድረግ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ውጤት አስገኝቷል

ባህርዳር፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የዳኝነት አገልግሎትን ፍትሐዊና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ተግባራዊ የተደረገው የሪፎርም ስራ ውጤታማ  መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ።

"የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፤ አገልግሎትን ማላቅ" በሚል መሪ ሐሳብ ለ10 ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች 2ኛው ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።


 

ፕሬዝዳንቱ አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት የዳኝነት ሥርዓቱን ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሪፎርም ተካሂዷል።

ሪፎርሙ ተግባራዊ በማድረግም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች  በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳዩት መሻሻል እና ለውጥ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

ፍርድ ቤቶች ተቀራራቢ በሆነ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እና ለዚህ የሚሆን ቁመና ላይ እንዲገኙ ለማድረግም በትኩረት ሲሰራ እንደነበር አመልክተዋል።

የክልሉ ፍርድ ቤቶች ከተደራሽነት፣ ከዲጂታላይዜሽን፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከቅልጥፍና እና አመቺ የሥራ ቦታ ከመፍጠር አንጻር እመርታዎች ማሳየታቸውን አስረድተዋል።

ዜጎች ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ዲጂታላይዜሽንን ማጠናከር እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የዳኞችን ሙያዊ ሥነ ምግባርና ክህሎት በማሳደግ ነፃ፣ ከአድሎና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ፍትሕን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ነው አቶ ቴዎድሮስ ያብራሩት።

የዲጂታል አሠራርን ወደ ታች በማውረድ ሁሉንም ሕብረተሰብ የፍትሕ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።


 

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው በበኩላቸው የዳኝነት አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ እየተከናወነ ባለው ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

የፍርድ ቤቶችን የአገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን፣ ፍትሐዊና ተአማኒነት ያለው ለማድረግ የተጀመረውን የሪፎርም ሥራ ዳር ለማድረስ በተለይ ትኩረት  እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም