ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የምታደርገው ጥረት ለቀጣናው ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የምታደርገው ጥረት ለቀጣናው ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው
ዲላ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ባለቤት ለመሆን እያደረገች ያለው ጥረት ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያን ባህር በር ባለቤትነት ለማሳካት በተለያየ መስክ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውንም ምሁራኑ አረጋግጠዋል።
በሰጥቶ መቀበል መርህ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ባለቤት ለመሆን እያደረገች ያለው ጥረት ለቀጣናው ሰላም መጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉም ምሁራን ገልጸዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ገመቹ ኦላኒ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሴራ የባህር በር ባለቤትነቷን ማጣቷን አንስተዋል።
ያጣቸውን ሃብቷን መልሳ ለማግኘት በሰላማዊ መንገድ የምታደርገውን ጥረት ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ተረድቶ ድጋፉን እያሳየ መምጣቱን አስረድተዋል።
በተለይ በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ በጋራ ተጠቃሚነትና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ የባህር በር ባለቤት ለመሆን እያደረገች ያለው ጥረት ዓለም አቀፍ ህግን ያከበረ ከመሆን ባለፈ ለቀጣናው ሰላም ያላትን ፍላጎት ያሳያል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለዜጎች የዘመናት ቁጭት ምላሽ የሚሰጥ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ማስረሻ ኤራጓ (ዶ/ር) ናቸው።
ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችበት መንገድ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸው፣ የተፈጥሮን ሃብት በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ የመጠቀም ዓለም አቀፍ የሕግ ድጋፍ ጭምር እንዳላት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ መንግስትና ህዝብ እያደረጉ ያሉትን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው የገለጹት ፕሮፌሰር ማስረሻ (ዶ/ር)፣ ለዚህም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።