ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ የልማት ጉዞዋ እና በቀዳማይ ልጅነት ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካ አዲስ የተስፋ ምዕራፍ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ የልማት ጉዞዋ እና በቀዳማይ ልጅነት ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካ አዲስ የተስፋ ምዕራፍ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ የልማት ጉዞዋ እና በቀዳማይ ልጅነት ልማት ያስመዘገበችው አስደናቂ ስኬት አፍሪካን ሊያስተሳስር የሚችል አዲስ የተስፋ ምዕራፍ ነው ሲሉ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሸቲማ ገለጹ።
በናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሸቲማ የሚመራ ሉዑክ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል።
ልዑኩ በዛሬው እለት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በህጻናት እድገትና በከተማ ልማት ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መድረክ አካሂደዋል፡፡
የናይጄሪያው ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሸቲማ በውይይቱ ወቅት፤ ስለኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ ውጤታማ የልማት ሥራዎች እንዲሁም በቀዳማይ ልጅነት ልማት ለተመዘገበው ውጤት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እድገት የሚታይና የሚጨበጥ መሆኑን በመጠቆም የኢትዮጵያ መንግሥት ለልጆች እንክብካቤ እና ለቀዳማይ ልጅነት ልማት የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችና የሕፃናት እንክብካቤ አሰራሮች ለብዙዎች ሕይወት መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝባቸው ተጠቃሚነትና ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተው መሥራታቸውንም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አወድሰዋል።
ናይጄሪያ እና ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ በመስራት አወንታዊ ተጽዕኖ መፍጠር ከቻሉ ይህ ክፍለ ዘመን የአፍሪካ ክፍለ ዘመን እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካ ከቀድሞው የግብርና እና የኢንዱስትሪ ዘመን አልፋ አሁን በእውቀት ላይ በተመሰረተው ሰው ሰራሽ አስተውሎትና በትላልቅ መረጃዎች ዘመን ውስጥ እንድትገባ የወጣቶችን አእምሯዊ አቅም ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የናይጄሪያ መንግሥትና ሕዝብ ውጤታማ ከሆኑ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ለመማር እና ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።