ቀጥታ፡

የመንግሥት እቅዶችና የወደፊት ትልሞች የዜጎችን ህይወት መለወጥ የሚያስችሉ ናቸው

አምቦ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ) ፦ የመደመር መንግሥት የያዛቸው እቅዶችና የወደፊት ትልሞች ሀገርን ከድህነት የሚያወጡና የዜጎችን ህይወት መለወጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በብዝሃ ዘርፍ እየተመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከስብራት ወደ እድገትና ማንሰራራት እያመራ መሆኑን ተጨባጭ ውጤቶቹ ያመላክታሉ።

በግብርና ዘርፍ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ያለፈ የስንዴ ምርት ማምረት የተቻለበት፤ የቡና ምርት በታሪክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የተገኘበት እንዲሁም የማእድን ዘርፍ የሀገር ኢኮኖሚ አቅም ሆኗል።

በቱሪዝም፣ ዲጅታላይዜሽንና የኢንዱስትሪ ዘርፍም የሚታዩና የሚጨበጡ ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑ ይታወቃል። 

በኢትዮጵያ አጠቃላይ ምጣኔ ሃብትና የልማት እንቅስቃሴ በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በብዝሃ ዘርፎች የሚታዩ ውጤቶች እየተመዘገቡ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ኃብት መምህር ታደለ መላኩ (ደ/ር)፤ በመደመር መንግስት በተለይም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማእድን፣ ዲጅታላይዜሽንና ሌሎችም እየተመዘገበ ያለውን ስኬት አድንቀዋል።

በአዳዲስ ኢንሸቲቮች እየታገዘ የቀጠለው የግብርና ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እራስን የመቻል እቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

በስራ እድል ፈጠራ፣ በከተሞችና የገጠር ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት እመርታዊ ስኬት መመዝገቡንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የመደመር መንግሥት የያዛቸው እቅዶችና የወደፊት ትልሞች ሀገረን ከድህነት የሚያወጡና የዜጎችን ህይወት መለወጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ናኦል በቀለ (ዶ/ር)፤ በዲጅታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የመጣው ለውጥና የተመዘገበው ስኬት ብዙ ሊባልለት የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

በጥቂት ዓመታት የዲጅታል ልማት ስትራቴጂው በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ፣ በፋይናንስ ተቋማትና ሌሎችም ሴክተሮች ላይ ያመጣውን ፈጣን ለውጥ በቀላሉ ማየት አይቻልም ብለዋል።

በመተግበር ላይ የሚገኘው ዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 በዘርፉ ትልቅ እመርታ የሚያመጣ መሆኑን በማንሳት በዚህ ረገድ የመንግስትን ተግባራዊ እንቅስቃሴ አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም