ቀጥታ፡

ካለመችው ሸብረክ የማትል ኢትዮጵያ፤ ወጥቶ መግቢያ በሯን ታስከብራለች!!

በቤተልሔም ባህሩ

ኢትዮጵያ የክንደ ብርቱዎች ምድርና የነጻነት ተምሳሌት መሆኗን ታሪክ ደጋግሞ ከትቦታል። በየዘመናቱ የተጎናጸፈቻቸው አኩሪ ገድልም የአፍሪካ ቀንዲልነቷን ደጋግማ እንድታረጋግጥ አስችለዋታል። ፈተናን ወደ ድል ተግዳሮትን ወደ ዕድል የምትቀይር በሕብርና ትብብር የተሸመነ አይበገሬ ሀገር መሆኗንም ታሪክ መዝግቧል፤ እየመዘገበም ይገኛል።

ቅድመ አያቶቻችን በዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ ባበሩት የነጻነት ጮራ የፈነጠቀው የድል ችቦ ለጭቁን የዓለም ሕዝቦች የነጻነት ተስፋን አብስሯል። ከዚያ የድል ታሪክ የተሸጋገረው የኢትዮጵያውያን አርበኝነትም በዚያ የሚያበቃ አይደለም። በእያንዳንዱ የትውልድ ምዕራፍ አዲስ የታሪክ ገጽ እየተጻፈ ቀጥሏል።

ከጉሊት ነጋዴ እናት እስከ ሀገር ጠባቂ ሰራዊት፣ ከጎልማሳ እስከ ታዳጊ፣ ከሀገር ውስጥ እስከ የተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጋራ ትጋትና ተሳትፎ የሀገራቸውን የልማት ሕልም እውን ለማድረግ የሚደርጉት ጥረት የዚህ ትውልድ አይበገሬነት መገለጫ ነው። በዚህ የጋራ ጥረት ውስጥ በጉባ ተራሮች ግርጌ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕዝብ ትብብርና የብሔራዊ ቁርጠኝነት ተጨባጭ ተምሳሌት ሆኗል። በጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የተመረቀው ሕዳሴም የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ የሚያሳልጥ አቅም ፈጥሯል። ለአፍሪካውያኑም በራሳቸው አቅም ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚችሉ የሚያመለክት የፓን አፍሪካኒዝም ሐውልት ሆኗል።

የመደመር መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት የሚያደርገው ጥረትና የሚያሳየው ቁርጠኝነትም ኢትዮጵያ ህልሟን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ያላትን ጽኑ ፍላጎት ያመላክታል። በሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ወቅት የሕዳሴ ግድብ የዘመናችን ትውልድ የአይበገሬነት ማሕተም መሆኑ መገለጹም ይህንኑ ያረጋግጣል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት ድጋሚ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሰየማቸውን ተከትሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ካለመችው ትልም ሸብረክ ሳትል ዕድገቷን የምታስቀጥል ሀገር መሆኗን ገልጸዋል። 

ባለፉት ዓመታትም በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያፋጥኑ መሰረቶችን በመጣል ሀገርን የሚቀይሩ የልማት ትሩፋቶች መፍጠር መቻሉንም አብራርተዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የቸራትን የውሃ ሀብት በራሷ ጥረት ለማልማትና ለመጠቀም ያጋጠሟትን ፈተናዎች በመሻገር ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን ማድረግ መቻሏን አንስተዋል። 

የግድቡ ስኬት የሀገሪቱን የኃይል ምርት አቅም ከማሳደግ ባሻገር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኃይልና በቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያሳልጥ ዕድል ይፈጥራል። ይህም የመደመር መንግሥት በጋራ ተጠቃሚነትና በትብብር ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫን እመርታዊ ጉዞ ያመለክታል።

ከሕዳሴ ግድብ ተሞክሮ በመነሳት ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መሻቷንም በሰላማዊ የዲፕሎማሲ ድርድርና በጋራ ጥቅም መርህ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው። ለኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎትና ቀጣናዊ ትስስር ጋር የተቆራኘ ስትራቴጂክ የሕልውና ጉዳይ ነው።

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት ካነሷቸው ዐበይት የልማትና የዕድገት ጉዳዮች አንዱ የባህር በር ጉዳይ ነው።

ጎረቤቶቻችን በተፈጥሮ ያገኘናቸው ወዳጆቻችን ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ከሁሉም ጎረቤቶች ጋር በሰላም ፣ በጋራ ጥቅምና በትብብር የመስራት መርሃችንን እንገፋበታለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ስልጣኔ ያለ ባህር በር እውን ሊሆን አይችልምና በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተን እንሰራለን ሲሉ አስምረውበታል።

በዚህም የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የዓለምና የአካባቢያችን ወቅታዊ ሁኔታ ብሎም የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ኃይል በመገንባት በቀጣናው የአየር የበላይነት ለመፍጠር የሚያስችል አቅም እንደሚገነባ አስታውቀዋል።

የሚኖረን መከላከያ ዘመናዊ፣ ፈጣሪ፣ ሁሌም ዝግጁ ብቁና ንቁ በየአውዶቹ የመሰማራት አቅምና ቁመና ያለው እንደሚሆን በመጠቆም፤ ችግሮች ሳይፈጠሩ በፊት አስቀድሞ ማወቅና መግታት ከመጡም መከላከል ከባሰም እንደ አባቶቹ እንደልማዱ ማሸነፍ የሚችል ኃይል ሆኖ ይገነባል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ውጭ ግንኙነት ማዕከላዊ መርህ ብሔራዊ ጥቅምና የዜጎች ክብር መሆኑን አንስተዋል። 

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ቀራጭነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንዲሸጋገር የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊ ምርጫዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አብራርተዋል።

በድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር በር የማግኘት መሻቷን በሰላማዊ መንገድ ማሳካት የውጭ ግንኙነቷ ትኩረት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በዚህም መንግሥት በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቶቿን በፍትሐዊነት የመጠቀም መብቷን እንድታረጋግጥና የባሕር በር ጥያቄዋን በጋራ ጥቅምና በሰላማዊ ድርድር እንደምታሳካ ገልጸዋል።

ይህ አቋም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከጋራ ሰላምና ደኅንነት ጋር በማጣጣም በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለውን ፍላጎት ያመለክታል። የዓባይን ውሃ በፍትሐዊነት የመጠቀም ቀጣይ መሻት፣ አስተማማኝ የባሕር በር የማግኘት ጥረት፣ ብሔራዊ ደኅንነትን ማረጋገጥና የዜጎችን ክብር የማስቀጠል ጥረት በሕዝብ ተሳትፎ፣ በመንግሥት ተቋማዊና በዜጎች አንድነት የሚጠናከሩ የጋራ ግቦች ናቸው።

በመሆኑም የሕዝብ ትጋትና የመንግሥት ጥረት የኢትዮጵያን ትልቅ ሀገርነት፣ የሕዝቧን ታላቅነትና የሰነቀችውን ታላቅ ርዕይ እውን የሚያደርጉ ዋነኛ መሠረቶች ናቸው። የጠንካራ ሀገር መንግሥት ግንባታ ሂደት የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ተሳትፎ፣ የተቋማትን ብቃት፣ የሕዝብን ትጋትና የትውልድን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ የጋራ ጉዞ ነው። 

ስለሆነም ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን በማጎልበትና በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ በመተባበር የሀገራችንን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት መወጣት ግድ ይለናል። የዘመኑ አርበኛ ትውልድም ከቀደሙት አያቶች የወረሰውን የነጻነትና የክብር ታሪክ በእውቀት፣ በሥራና በልማት በማላቅ ብሔራዊ ጥቅምና የዜጎችን ክብር ለማስከበር የሚጠይቀውን የጋራ ጥረትና ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል። 

ኢትዮጵያም የትናንትን መሰረት አጽንታ፣ የዛሬን አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር ለተሻለ ነገ ትሰራለች። ምክንያቱም የትልቅ ሀገር ታላቅነት የሚረጋገጠው ከታሪክ ባሻገር በሕዝብ የጋራ ትጋት፣ በመንግሥት ተቋማዊ ጥረትና በትውልዱ የጋራ ቁርጠኝነት በሚገነባው የወደፊት ስኬትም ጭምር ነው።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ የሰነቀችው ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መሻቷንም በሕዝብና በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ታሳካለች። የዘመኑ አርበኛ ትውልድ ብሔራዊ ጥቅሙንና ክብሩን ለማስጠበቅ መትጋት ይጠበቅበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም