የኢትዮጵያ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ - የመደመር መንግሥት እሳቤ ትሩፋቶች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ - የመደመር መንግሥት እሳቤ ትሩፋቶች
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
የመደመር መንግሥት እሳቤ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የልማት አቅጣጫዎችን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ እያሸጋገረ ይገኛል። በዚህም በግብርና ዘርፍ ብቻ ተወስኖ የቆየውን የኢኮኖሚ መሰረት ወደ ባለብዙ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት ለማስፋት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በዚህም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በተከናወኑ በርካታ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
የመደመር መንግሥት ምሥረታና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት፣ አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ የሰየመ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሀገሪቱ የልማት ስኬቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የበጋ መስኖ ልማትና የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሮች የስንዴ፣ ሩዝ፣ ወተትና እንቁላል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ እያሳኩ መሆኑን፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ በዲጂታሉም የፋይዳ ማንነት፣ የገበታ፣ የወንዝ ዳርና የማዕድን ልማት ፕሮጀክቶችም የምርትና አገልግሎት አሰጣጥ ባህልን ወደ ላቀ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር አንስተዋል።
የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራና ስኬቶቹ
የመደመር መንግሥት እሳቤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እና ውጤቶችም እንዲመዘገቡ እያስቻለ ይገኛል። በዚህም በግብርና ዘርፍ በዘመናዊ የመስኖ ልማት፣ በበጋ ስንዴ ምርት እና በኩታ-ገጠም የአስተራረስ ዘዴዎች የተገኙ ውጤቶች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በተጨማሪም በሌማት ትሩፋት፣ በከተማ ግብርና፣ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት መጨመርና ሌሎች ውጤታማ ተግባራትም ተከናውነዋል።
በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ በሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለዜጎች በተለይም ለወጣቶችና ለሴቶች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እየፈጠረ ይገኛል። በመደመር መንግሥት እሳቤ በመመራት በዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙት ውጤታማ ተግባራት ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ከማቅረብ አንጻርም አበርክቷቸው ከፍተኛ ሆኗል።
ከሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግብርና ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ ይህን ዘርፍ ማዘመን፣ ሜካናይዜሽንን ማስፋፋትና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የኢትዮጵያን የልማትና የዕድገት ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ መንገድ ነው።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ ሀገራዊ የማምረት አቅምን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ እና ለማዳን እንዲሁም ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ ሀገራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል። ለዚህ እንደጥሩ ምሳሌ የሚጠቀሰው በስፋት ተተግበሮ ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡበት የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ነው። ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ በዘርፉ ለዓመታት ተግዳሮት ሆነው የቆዩ ጉዳዮችን በመፍታት ተጨባጭ ለውጦችን በማምጣት የሀገሪቱን የማምረት አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አስችሏል።
የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ በተወሰዱ ተግባራዊ እርምጃዎች አሁን ላይ የማምረት አቅማቸው ከ69 በመቶ በላይ ማደጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ መግለጻቸው የንቅናቄውን ውጤታማነት በግልጽ የሚያመላክት ነው።
ንቅናቄው ተዘግተው የነበሩ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ የሰው ኃይል እንዲሰባሰብና ምርታማነት እንዲያድግ በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። ቀደም ሲል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረትም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማዳን ተችሏል። ለዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማስፋፋትና ማጠናከር፣ ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች አቅም እንዲጎለብት በተሰራ ስራም እንዲሁ ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ መደረጉ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
የመደመር መንግሥት በኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲመዘገብ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ስኬታማ ለማድረግ በርካታ የፖሊሲ እና የአሰራር ማሻሻያዎችን አድርጓል። በዚህም የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን የሚጨምሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እና የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ማሻሻያዎች ተደርገዋል። እነዚህ የተግባር እርምጃዎች የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱ እንዲጨምርና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ አስችለዋል።
የመደመር መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው እና ውጤቶች ካስመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል የዲጂታል ዘርፍ ተጠቃሽ ነው። ይህ ዘርፍ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ካለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንጻር የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ተቀርጾ ተግባራዊ ተደርጓል። ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ተደርጎ የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገቡ ይታወቃል። በዚህም ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ 2025 የኢትዮጵያን የልማትና የዕድገት ጉዞ በማፋጠን፣ ሀገሪቱን በቴክኖሎጂ ወደሚመራ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ አዲስ የዕድገት ሞተር ነው።
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠናቀቂያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር ላይ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ የተሳካ ነው" ሲሉ መግለጻቸው። ይህም ብቻ ሳይሆን ከአምሥት ዋና ዋና ዘርፎች መካከል አንዱ ስትራቴጂ መሆን አለበት ለኢትዮጵያ ብልጽግና አይተኬ ሚና አለው ነው ያሉት።
ዲጂታል ቴክኖሎጂ የመደመር መንግሥት ለነደፋቸው ሌሎች ዋና ዋና ዘርፎች ውጤታማነትም አጋዥ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝና ለበርካታ ወጣቶች ሰፊ የሀገር ውስጥ እና የውጭ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው።
በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘረፍ እየተገኙ ካሉ ውጤቶች መካከል የፋይናንስ ዘርፉን ቀልጣፋ እያደረገ መምጣቱ ተጠቃሽ ነው። በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ዲጂታል የክፍያ ስርዓትን በመጠቀም ግብይት እየፈጸሙ መሆኑ ለውጤታማነቱ ጥሩ ማሳያ ነው። የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን መቀነስ፣ ሥራንና ንግድን ማቀላጠፍ እንዲሁም ሰዎች ገንዘብ በሚያስፈልጋቸው ጊዜና መጠን እንዲጠቀሙ እያስቻለ ይገኛል። ይህም ከባንክ ውጭ የሚዘዋወር የገንዘብ መጠንና የህትመት ወጪ እንዲቀንስና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲጨምር አስችሏል። ከዚህ አኳያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፉ እንዲመጣ የታቀደው ግብ እየተሳካ ነው።
በፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያና መሶብ የአንድ ማዕከል የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ለማስፋት በተሰራ ስራ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል። እነዚህ ወሳኝ የመንግስት ውሳኔዎች የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት ምህዳርን በመፍጠር ዜጎች አገልግሎቶችን ፈጣን፣ ግልጽ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ እያስቻሉ ይገኛሉ። እነዚህ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራር ስርዓቶች አገልግሎት ለማግኘት ይባክን የነበረውን ጊዜና ወጪ ከመቀነሳቸው ባለፈ ቢሮክራሲንና ብልሹ አሰራረን በመቀነስ በኩል ከለፍትኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
በመደመር መንግሥት እሳቤ ከተገለጡ የሀገር ሀብቶች መካከል ለቱሪዝም ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የተገኙ አመርቂ ስኬቶች ይጠቀሳሉ። በዚህም አቧራ ለብሰው የቆዩ እና ለቱሪዝም መስህብነት ቢውሉ ከፍተኛ ጠቀሜታ የነበራቸውን ሀገራዊ ሀብቶች በመግለጥና በማልማት ወደ ወረት የተቀየሩበት አስደማሚ ስራዎች ለዚህ ትልቅ ማሳያዎች ናቸው።
ይህ ውጤታማ ተግባራም ዘርፉ እንዲነቃቃ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲያድግ በር ከፍቷል። በዚህም ኢትዮጵያ በባለፈው 2018 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች። በሌላ በኩል ለበርካታ ዜጎችን ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በመላ ሀገሪቱ ለመሠረተ ልማት መስፋፋት የተሰጠው ትኩረትም የከተሞች ውበትና መስህብነት እንዲያድግ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በዚህም የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ፍሰት ጨምሯል። ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ማደግም እንዲሁ አስተዋጽኦው የጎላ ነው። የየአካባቢዎቹ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ተነቃቅተዋል። የኢትዮጵያም የቱሪዝም ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲጎላ አስችሏል።
የመደመር መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ለማዕድን ልማት እንዲሁ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚያስችል ምህዳር ተፈጥሯል። ባለፉት አመታት ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል። ቀደም ሲል በጥሬው ወደ ውጭ ይላኩ የነበሩ የወርቅ፣ ድንጋይ ከሰል፣ ኦፓልና ሌሎች ማዕድናት ላይ እሴት ተጨምሮባቸው ለወጪ ንግድ እንዲውሉ ለማድረግ አዳዲስ አሰራሮች በመዘርጋታቸው ስኬቶች ተመዝግበዋል።
ለአብነትም ከወርቅ ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ በከፍተኛ መጠን አድጓል። ለምሳሌ በ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከወርቅ ወጪ ንግድ ከ5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች። በሲሚንቶ፣ ድንጋይ ከሰል፣ ሴራሚክ ምርቶች ለኢንዱስትሪና ለግንባታ ዘርፍ ግብዓት በመሆን በርካታ ፋይዳዎች ተገኝተዋል። የማዕድን ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራና የአካባቢ ኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በጥቅሉ የመደመር መንግሥት የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ የቱሪዝም እና የማዕድን ዘርፎች ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የየድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል የወሰዳቸው የፖሊሲ እና የስትራቴጂ እርምጃዎች ሀገሪቱ በአዲስ የዕድገት አቅጣጫ እንድትጓዝ እያስቻላት ይገኛል። ይህም ለወጭ ንግድ የሚሆኑ ምርቶች በስፋት እንዲመረቱ፣ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በዚህም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግና ለማዳን እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ስራዓት በማዘመን፣ ሀገሪቱ ዘላቂና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ብልጽግና እንድታስመዘግብ ጠንካራ መሠረት ጥሏል።