ቀጥታ፡

የከተሞች ትንሳኤ ምሥጢር - የመደመር መንግሥት 

በታዬ ለማ

👉አዲስ አበባ ዳግም አብባለች

ጎህ ሲቀድ በአዲስ አበባ ላይ የሚወጣው ፀሐይ ዛሬ ሌላ ከተማ ያበራል። ሰፋፊ መንገዶቿ ላይ ብርሃን ሲያርፍ፣ በእግረኛ መንገዶቿ ላይ የማለዳ ተጓዦች ሲተላለፉ፣ በወንዞቿ ዳርቻ የተሠሩ ፓርኮች አረንጓዴ ሲለብሱ ማየት ይቻላል። ይህች ከተማ እንደ ስሟ አዲስ ሆናለች። ይህ ለውጥ ግን ድንገት የመጣ አይደለም፤ በትልቅ ቁጭት  የተገነባ የትውልድ ተሻጋሪ አሻራ ነው፡፡

👉አገር እየተቀየረች ነው

የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት አገርን የሚቀይሩና ኢትዮጵያን ወደ ፊት ያራመዱ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል።

በኢኮኖሚው ዘርፍ ታሪካዊ ውጤት ተመዝግቧል። ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ የምታስገባ አገር መሆኗ ቀርቶ ዛሬ ወደ ውጭ የምትልክ ሆናለች። በኢንዱስትሪው ዘርፍም ትልቅ ድል ተገኝቷል፤ ቀደም ሲል ብዙ የውጭ ምንዛሬ ያስወጡ የነበሩ ምርቶች አሁን እዚሁ ይመረታሉ፤ በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።

በማዕድን ዘርፍ እስከ ዛሬ ታይቶ በማያውቅ መንገድ የኢትዮጵያ ማዕድናት እንዲወጡ እየተደረገ ነው፤ አገሪቱም ከዚህ ሀብቷ ተጠቃሚ እየሆነች ነው። በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሠሩት ሥራዎች አስደናቂ ናቸው፤ መንግሥት በቴክኖሎጂ የተገነባች የነገዋን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ምን ያህል ርቀት እንደተጓዘ ያሳያሉ።

በቱሪዝም ዘርፍ ደግሞ «ገበታ ለሀገር»፣ «ገበታ ለሸገር» እና «ገበታ ለትውልድ» በተሰኙ ማዕቀፎች አስደናቂ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚህ ሳቢያ አብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች በአስደናቂ ሁኔታ ተቀይረዋል። ታሪካቸው ተለውጦ አዲስ መልክ የያዙት እነዚህ ስፍራዎች ለዜጎቻቸው ኑሮ የተመቹ ከመሆናቸውም በላይ የውጭ አገር ዜጎች ጭምር ሊጎበኟቸው የሚናፍቋቸው ከተሞች እየሆኑ ነው። ከእነዚህ ሁሉ መካከል እንደ ስሟ በመደመር መንግሥት ዘመን አዲስ መሆን የቻለችው አዲስ አበባ ጎልታ ትታያለች።

👉«ውብ አበባ» የተባለችው አገር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛው የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ይህንኑ እውነታ አንስተዋል። ከተሞቻችን የዘመናዊ ከተማ መልክ ለመያዝ በጀመሩት ጥረት ለመኖሪያ የተመቹ፣ ለንግድና ለኮንፈረንስ የተስማሙ፣ ተምሳሌት ተደርገው የሚጠቀሱም እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

«ዛሬ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ውብ አበባ ተብላ ብትጠራ እውነት እንጂ ባዶ ምኞት ተደርጎ አይወሰድም» ብለዋል።

አያይዘውም የአዲስ አበባ ለውጥ የዓለም ጎብኚዎችን «ኑ ወደ እኔ» እያለ የሚጣራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት እውነት ነው።

👉ትናንት የነበረችው አዲስ አበባ

ይህ ጥሪ ምን ያህል ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ለመረዳት ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና፣ የአፍሪካም የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና ለዘመናት በአገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ቦታ ይዛ ኖራለች። ይሁን እንጂ እድገቷ ከደረጃዋ ጋር ፈጽሞ አይጣጣምም ነበር።

በአብዛኞቹ የከተማዋ ክፍሎች ደረጃውን የጠበቀና ከተሽከርካሪ መንገድ የተለየ የእግረኛ መንገድ አልነበረም። እግረኛው ከመኪና ጋር እየተጋፋ ይጓዝ ነበር፤ መንገዶቿም ለትራፊክ አደጋና ለእግረኞች እንግልት ዋና ምክንያት ነበሩ። የመንገድ ዳር መብራቶች ካሉበት ቦታ ይልቅ የሌሉበት አካባቢዎች በርከት ይሉ ነበር፤ በርካታ አደባባዮችና መንገዶችም ከፍተኛ ጥገና ይፈልጉ ነበር። ዘመናዊና አማራጭ የትራንስፖርት ዘዴዎችን የሚያበረታቱ መንገዶች ደግሞ ጨርሶ የሚታሰቡ አልነበሩም።

ሌላው ጎልቶ የሚታይ ክፍተት የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች እጥረት ነበር። ነዋሪው ነፃ ጊዜውን የሚያሳልፍበት ሰፊ ቦታ አልነበረውም። በከተማዋ ውስጥ አቋርጠው የሚያልፉ በርካታ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎችም ተንከባካቢ በማጣታቸው በቆሻሻ ተሞልተው የአካባቢ ጥበቃ ሥጋት ሆነው፣ የበሽታ ምንጭና የደህንነት ስጋትም ነበሩ፡፡

እንደ ካዛንቺስና አራት ኪሎ ባሉ የከተማዋ እምብርት ሰፈሮች ውስጥ በአንድ ወቅት ተደራርበው የቆሙ አሮጌ የጭቃ ቤቶች፣ ጠባብ ጥጋጥጎች እና የታጨቁ መንደሮች የተለመደ ገጽታ ነበሩ። የዘመናት ታሪክ የተሸከሙ ሕንፃዎችና መኖሪያዎች ተገቢውን እድሳትና እንክብካቤ ሳያገኙ በጊዜ ሲሸረሸሩ ኖረዋል። ከተማዋ ወጥ የሆነ የውበትና የቀለም መመሪያ ስላልነበራት ገጽታዋ የተበታተነ ነበር፤ የታሪካዊ ስፍራዎችና የሐውልቶች ዙሪያም በቂ ጽዳትና ብርሃን አላገኘም ነበር።

ዛሬ ግን ያ ገጽታ ወደ ታሪክነት እየተሸጋገረ ነው። እነዚሁ ሰፈሮች በዘመናዊ ዕቅድ ተቃኝተው፣ ታሪካዊ ሕንፃዎቻቸው ታድሰውና ተጠብቀው፣ በተዋሃደ የቀለምና የዲዛይን ቅንብር አዲስ መልክ እየያዙ ነው። ሐውልቶችና ታሪካዊ ስፍራዎች በጽዳትና በምሽት ብርሃን ተውበው፣ ለነዋሪው ኩራት ለጎብኚውም መስህብ ሆነው ይታያሉ።

👉ትንሳኤ

ዛሬ ግን ታሪኩ ተቀይሯል።

አዲስ አበባ የትናንት ገጽታዋን በማይታመን ሁኔታ እየቀየረች ነው። ነዋሪው ለውጡን እያጣጣመው ነው፤ ዓለምም አድናቆቱን እየገለጸ ነው። ትናንት የነበረችው አዲስ አበባ ላትመለስ ተሰናብታለች። መዓዛዋ ተቀይሯል፤ ደስ የማይል ገጽታዋና ሽታዋም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዷል። አዲስ አበባ በእርግጥም አዲስ ሆናለች።

👉የመደመር መንግሥት ለአዲስ አበባ ትንሳኤ ሆኗታል።

ዛሬ እንደ ስሟ አዲስ ሆና ተገንብታለች። በኮሪደር ልማቷ፣ በስማርት ሲቲ ግንባታዋና በሰው ተኮር ልማቶቿ ለዜጎቿ ምቹ እየሆነች፣ የአፍሪካ መዲናነቷንም በትክክል እያረጋገጠች ትገኛለች። የኮሪደር ልማት አዲስ አበባን ከጊዜው ጋር የሚመጥንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሠረተ ልማት ባለቤት ያደረገ ትልቅ የለውጥ ምዕራፍ ነው። ፕሮጀክቱ መንገድን ከማሻሻል ባለፈ የከተማዋን ሁለንተናዊ ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይሯል።

👉ከመንገድ እስከ እግረኛ

የከተማዋ ዋና ዋና አውታሮች ሰፊና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው እንደገና ተገንብተዋል። ተሽከርካሪዎች ቀልጣፋ ፍሰት አግኝተዋል፤ የትራፊክ እንግልትም በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ቀሏል።

ቀደም ሲል ትኩረት ተነፍጎት የነበረው እግረኛ አሁን ትክክለኛውን የመራመጃ ቦታ አግኝቷል። የእግረኛ መንገዶች ተስፋፍተዋል፤ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መተላለፊያዎች፣ ንጹሕና ውብ የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም የብስክሌት መጋለቢያ መስመሮች ተካተዋል። ዜጎች ደኅንነታቸው በተጠበቀ፣ ምቹ በሆነ አካባቢ መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ምሽት ሲመጣም ከተማዋ አትደበዝዝም። ዘመናዊና ኃይል ቆጣቢ የመብራት ሥርዓቶች፣ የዲጂታል መረጃ መስጫ ሰሌዳዎችና ውብ የመንገድ ዳር አረንጓዴ ልማቶች ውበቷንና ደኅንነቷን ይጨምራሉ። ይህ የተቀናጀ ልማት አዲስ አበባን የነዋሪዎቿን ፍላጎት የምታሟላ፣ ለኑሮና ለሥራ ምቹ፣ የአፍሪካ መዲናነቷንም በሥራ ያረጋገጠች ዘመናዊ ከተማ አድርጓታል።

👉ወንዞችና አረንጓዴ ስፍራዎች

በአንድ ወቅት የቆሻሻ መጣያና የከተማዋ ሥጋት የነበሩት የወንዝ ዳርቻዎችና ክፍት ቦታዎች ዛሬ የከተማዋ ዋነኛ የመስህብ ሀብትና የጽዳት ማዕከል ሆነዋል። በከተማዋ ማዕከልና አካባቢ የሚያልፉ ጥንታዊ ወንዞች ከቆሻሻ ተነጥለው የተፈጥሮ ፍሰታቸውን ጠብቀው እንዲፈሱ ተደርገዋል። ዳርቻዎቻቸው በድንጋይና በኮንክሪት ግድግዳዎች ተጠብቀው ከጎርፍ ሥጋት ነፃ ሆነዋል።

በወንዝ ዳርቻዎች ላይ የተገነቡት ውብ ፓርኮች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎችና የስፖርት ማዕከላት ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ሁለንተናዊ የዕረፍትና የመዝናኛ አማራጭ ፈጥረዋል። የዛፎችና አረንጓዴ ተክሎች መብዛት የከተማዋን የአየር ጥራት አሻሽሏል፤ የሙቀት መጠኑን አመጣጥኖ የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳሩ እንደገና እንዲያንሰራራ አድርጓል። በዚህም አዲስ አበባ አረንጓዴ፣ ንጹሕና ለኑሮ እጅግ ተስማሚ ሆናለች።

👉ሰላምና ደኅንነት

የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበትና ገጽታ ብቻ አልቀየረም፤ ወንጀልን በመከላከልም ትልቅ ሚና እየተወጣ ነው። ፍትሕ ሚኒስቴር «የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በወንጀል መከላከልና ደኅንነት ማረጋገጥ ላይ ያለው ሚና» በሚል ርዕስ ባካሄደው ጥናት ይህንኑ አመልክቷል። በተለይ ለጎዳና ወንጀል ምቹ የነበሩ ስፍራዎች እንዲጠፉ በማድረግ አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ ዕድል መፍጠሩን ጥናቱ ያሳያል።

👉ጉዞው ይቀጥላል

ታላቅ ሕዝብን የሚመጥን ርዕይ የሰነቀችው ኢትዮጵያ፣ ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ይበልጥ የማደስ ተግባሯን አጠናክራ ትቀጥላለች። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማዋን ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለመምራት በተመረጡበት ወቅት ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው። በቀጣዮቹ ዓመታት አዲስ አበባን ይበልጥ ጽዱ፣ ሳቢ፣ ምቹና ለነዋሪዎቿ ተስማሚ የማድረጉ የሪፎርም ሥራ ተጠናክሮ  የሚቀጥል ነው በማለት አፅንኦት ሰጥታዋል።

ትናንት የነበረችው አዲስ አበባ ተሰናብታለች። ዛሬ የምትታየው አዲስ አበባ ደግሞ ገና ጅማሬዋ ላይ ናት።

👉አዲስ አበባ የለኮሰችው የልማት ችቦ በሁሉም ይበራል

ከአዲስ አበባ የተነሳው የልማት ብርሃን በዚያው አልተወሰነም፤ ወደ ሁሉም የአገሪቱ ማዕዘናት እየተሰራጨ ነው። በመዲናዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ፓርኮችና የከተማ እድሳት ልምድ ወደ ሌሎች ከተሞች ተሸጋግሮ፣ ዛሬ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ከተሞች አዲስ መልክ እየያዙ ይገኛሉ።

የመደመር መንግሥት የሚያከናውነው ልማት ማንንም ወደ ኋላ የማይተው፣ ሁሉንም አካባቢዎች በእኩል ዓይን የሚያይና ያቀፈ ነው። በ«ገበታ ለሀገር»፣ «ገበታ ለሸገር» እና «ገበታ ለትውልድ» ማዕቀፎች በተለያዩ ክልሎች የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ በየከተማው የሚታዩ ዘመናዊ መንገዶችና የመዝናኛ ስፍራዎች፣ እንዲሁም በገጠር የሚካሄዱ የግብርና እና የመሠረተ ልማት ሥራዎች አንድ እውነት ይናገራሉ፤ ልማቱ የአንድ ከተማ ሳይሆን የመላው አገር መሆኑን።

አዲስ አበባ ለሌሎች ከተሞች አርአያ ሆና ስትቆም፣ ሌሎች ከተሞችም በየፊናቸው አብበው የአገሪቱን ውበት እያበዙ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ በአንድ ማዕከል ብቻ የምታደምቅ ሳትሆን፣ በሁሉም ማዕዘኗ የምታበራ፣ ዜጎቿም በየትኛውም ቦታ የልማቱ ተካፋይና ተጠቃሚ የሆኑባት አገር እየሆነች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም