ቀጥታ፡

19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን የፊታችን ሰኞ ይከበራል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ)፦ 19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተገኙበት ይከበራል፡፡

“ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” ቀኑ የሚከበርበት መሪ ሐሳብ ነው።

የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሰኞ ይከበራል።

ይህ በዓል ኢትዮጵያውያን የሀገርን ዳር ድንበር እና ክብሯን ለማስጠበቅ ደምና ላባቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያስከበሩት ሰንደቅ ዓላማ በጋራ የሚከበርበት ቀን ነው።

ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ በዋናነት የኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫና አርማ መሆኑን ምክር ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል።

ቀኑ ለሠንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠት ዜጎች የጋራ እሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበትና በሀገራዊ አንድነትና ህብረ ብሔራዊነት መግባባትን የሚፈጥሩበት ሁነት ነው።

ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን መከበር ከጀመረ 18 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነትና አስተባባሪነት በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

በዚህም መሠረት የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ዕለቱን አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልዕክት በማስተላለፍ በንግግር ከከፈቱ በኋላ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አማካኝነት በቀጥታ ስርጭት በመላው ሀገሪቱ ዜጎች በሠንደቅ ዓላማው ፊት ቃለ መሃላ የሚፈጸምበት ሥነ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ማርሽ ባንድ እና ክብር ዘብ ታጅበው በፕሬዘዳንቱ አማካኝነት ሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት ይከናወናል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ።

ይህ በዓል በመላው ሀገሪቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች እንደሚከበር የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም