ሀገራዊ ብልፅግናን ከውጭ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ጋር የሚያስተሳስር አዲስ ምዕራፍ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ብልፅግናን ከውጭ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ጋር የሚያስተሳስር አዲስ ምዕራፍ
የመደመር መንግሥት- ሀገራዊ ብልፅግናን ከውጭ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ጋር የሚያስተሳስር አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ
ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበት ምዕራፍ በታሪኳ ውስጥ ልዩ ቦታ የሚይዝ ነው። በአንድ ወቅት በፖለቲካዊ ውጥረት፣ በኢኮኖሚያዊ ጫና፣ በማኅበራዊ መለያየት እና በተለያዩ ሀገራዊ ፈተናዎች የተከበበች ሀገር፣ ዛሬ በራሷ አቅም እና በራሷ እሳቤ በመመራት የዕድገትና ብልፅግና ግስጋሴ ላይ ትገኛለች። ይህ ስኬት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት በሕዝብ ፈቃድ ወደ ሥልጣን የመጣው አመራር በሀገር በቀል የመደመር እሳቤ ላይ ተመስርቶ ያከናወነው ጉዞ ውጤት ነው።
የመደመር ፍልስፍና እንደ ፖለቲካ መርህ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሀገር ግንባታ ስትራቴጂ ተቀርጾ የተተገበረ ነው። የዚህ እሳቤ አፍላቂ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ወቅቶች የተደቀኑ ውስብስብ ፈተናዎችን በመሻገር፣ ሀገሪቱን ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወደ መረጋጋት፣ ከመቆም ወደ መንቀሳቀስ፣ ከጥርጣሬ ወደ ተስፋ እና ከተግዳሮት ወደ ዕድል የመቀየር ቁርጠኛ አመራር አሳይተዋል። ዛሬ ኢትዮጵያ የምትናገረው ስለ ሕልውና ጥያቄ ሳይሆን፣ ስለ ብልፅግና፣ ስለ ከፍታ እና ስለ ቀጣይ ትውልድ ዕጣ ፈንታ ነው።
ይህን ለውጥ የሚመሰክሩ ተጨባጭ ውጤቶችም በስምንቱ ዓመታት ጉዞ በስፋት ተመዝግበዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሀገራዊ ሕልም ወደ ተጨባጭ እውነት በመቀየር የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎት እና የሕዝቧን ጽናት ለዓለም አስመስክሯል። የገበታ ለሸገር፣ የገበታ ለሀገር እና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ደግሞ የቱሪዝም ሀብቶችን ከጥላ ወደ ብርሃን በማምጣት፣ ተፈጥሮን፣ ታሪክን እና ልማትን አስተሳስረው ኢትዮጵያን አዲስ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን መሠረት ጥለዋል።
በተመሳሳይ ጊዜ ሀገሪቱ ከአንድ ዘርፍ ተመርኩዞ ከሚጓዝ ኢኮኖሚ ወደ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ የመሸጋገር ጉዞ ጀምራለች። በቱሪዝም ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ በማዕድን ዘርፍ የተፋጠነ እንቅስቃሴ፣ በግብርና የተመዘገበው የምርታማነት ዕድገት፣ በማኑፋክቸሪንግ የተፈጠሩ አዳዲስ አቅሞች፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ እና በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የተመዘገቡ ለውጦች ኢኮኖሚውን የበለጠ ተወዳዳሪ እና ዘመናዊ እያደረጉት ነው። ዲጂታል ኢትዮጵያ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርሞች፣ የኢንቨስትመንት መስክ ማሻሻያዎች እና የአምራች ኢንዱስትሪ ማስፋፊያዎች የሕዝብን ተጠቃሚነት በማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገትን ወደ ተጨባጭ ውጤት የቀየሩ ናቸው።
በከተማ ልማት የተመዘገቡ ለውጦችም የመደመር መንግሥት እሳቤን ከቃል ወደ ተግባር የቀየሩ ግልጽ ማሳያዎች ናቸው። በተለይም የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ከተሞችን ዘመናዊ፣ ማራኪ እና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምቹ በማድረግ የከተማ አኗኗር ዘይቤን በአዲስ መልክ እያሻሻሉ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ልማት ማለት የሕዝብን አኗኗር ማሻሻል፣ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ማስፋት እና የሀገርን ገጽታ መቀየር መሆኑን ያሳያል።
እነዚህ ተጨባጭ ውጤቶች በመሆናቸው ነው ሕዝቡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን በማሰብ ውሳኔ የሰጠው። የተጀመሩት ለውጦች እንዲቀጥሉ፣ የተገኙት ስኬቶች እንዲጠናከሩ እና የብልፅግና ጉዞው ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር በማመን ሕዝቡ የብልፅግና ፓርቲን በመምረጥ አዲሱ የመደመር መንግሥት እንዲመሠረት አድርጓል። ይህም ምርጫ የፖለቲካ ሂደት ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝብ በተጨባጭ ውጤቶች ላይ የሰጠው እምነት እና ድጋፍ ነበር።
በመሆኑም የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ የተመሠረተው አዲሱ የመደመር መንግሥት የአዲስ ካቢኔ ምሥረታ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ የከፍታ ምዕራፍ የምትሸጋገርበት ታሪካዊ መድረክ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመንግሥት ምሥረታ ወቅት በምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ያነሷቸው አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮችም ይህንን እውነታ ያረጋግጣል። ኢኮኖሚያዊ ለውጥ፣ የከተማ ልማት፣ የግብርና ምርታማነት፣ የስልጣኔ ግንባታ እና የተቋማት ጥንካሬ እንደ ዋና ዋና የልማት ምሰሶዎች ቀርበዋል።
በተለይም የሀገር ብልፅግና የሚገነባው በጠንካራ ኢኮኖሚ፣ በምርታማ ዜጎች፣ በዘመናዊ ከተሞች እና በጠንካራ ተቋማት መሆኑን በንግግራቸው አንስተዋል። ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት የምትከተለውን የልማት አቅጣጫም በግልጽ አመላክተዋል። ይህም በመደመር እሳቤ ላይ ተመስርቶ ልዩነቶችን ወደ ጥንካሬ፣ ችግሮችን ወደ ዕድል እና ሀብቶችን ወደ ብልፅግና የመቀየር መንገድ ያመላከተ ሆኗል።
አዲሱ የመደመር መንግሥት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ጠንካራ መሠረት እንዳለውም አረጋግጧል። ኢትዮጵያ በቀጣናው የምትጫወተውን ሚና ማጠናከር፣ የዲፕሎማሲ ተፅዕኖዋን ማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ጥቅሞቿን ማስከበር እና የባህር በር ባለቤት የመሆን ጽኑ ፍላጎቷን በሰላማዊ እና በተቀናጀ መንገድ ለማሳካት ጠንካራ የውስጥ አቅም ያስፈልጋል። ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ፣ ያለ ተቋማዊ ብቃት እና ያለ ሀገራዊ አንድነት ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስከበር አይቻልም። ስለዚህ የመደመር መንግሥት ምሥረታ የውስጥ ብልፅግናን ከውጭ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ጋር የሚያስተሳስር ታሪካዊ እርምጃ ነው።
በመሆኑም የመደመር መንግሥት ምሥረታ የፖለቲካ ክስተት ብቻ ሳይሆን፣ ከፈተና ወደ ዕድል፣ ከለውጥ ወደ ብልፅግና እና ከብልፅግና ወደ ከፍታ የሚወስደውን ሀገራዊ ጉዞ የሚያጠናክር አዲስ ታሪካዊ ውል ነው። ዛሬ የተጀመረው ጉዞ የአንድ መንግሥት ወይም የአንድ ትውልድ ጉዞ ብቻ አይደለም፤ የበለጸገች፣ የተረጋጋች፣ በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሙሉ ማስከበር የምትችል ኢትዮጵያ የመገንባት ታሪካዊ ሂደት ነው።