የመደመር መንግስት ቀጣይ ዕቅዶች እንዲሳኩ በጥናትና ምርምር ለማገዝ ዝግጁ ነን- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት ቀጣይ ዕቅዶች እንዲሳኩ በጥናትና ምርምር ለማገዝ ዝግጁ ነን- ምሁራን
ሀዋሳ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ) ፦የመደመር መንግስት በቀጣይ ለማከናወን ያቀዳቸውን ተግባራት ለማሳካት ብቁ ባለሙያ ከማፍራት ባሻገር በጥናትና ምርምር ሥራዎች ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የመደመር መንግስት በቀጣይ ዓመታት ጥራትን መሰረት ያደረገ ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመንግስት ምስረታ ወቅት ለምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር መግለጻቸው ይታወሳል።
በተለይ የትምህርት፣ የጤና እና የማህበራዊ ጥበቃን ዘርፍ ከስፋት ወደ ጥራት በማሸጋገር ዜጋን ማዕከል ያደረገ የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑም ተገልጿል።
የመደመር መንግስት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በአግባቡ እንዲተገበሩና ስኬታማ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር ብቁ ባለሙያ የማፍራትና የተለያዩ ችግር ፈቺ ምርምሮችን የማድረግ ሚናቸውን እንደሚወጡ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልፀዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት መምህርና ተመራማሪ ታፈሰ ማቲዮስ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት መንግስት ባከናወናቸው ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
ዩኒቨርሲቲውም የመደመር መንግስት በቀጣይ ለማከናወን የያዛቸው ዕቅዶች እውን እንዲሆኑ የሰለጠነ ሰው ሀይል ከማፍራት ባለፈ በመንግስት የትኩረት መስኮች ላይ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በመስራት የበኩሉን እንደሚወጣም ገልጸዋል።
ልማት ስኬታማ እንዲሆን የዜጎች ሚናም ከፍተኛ እንደሆነ ያነሱት ታፈሰ (ዶ/ር)፣ ህብረተሰቡም ለሀገራዊ ዕቅዶቹ መሳካት የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
የዲጅታላይዜሽን ትግበራ የመንግስትና የግል አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ከማድረግ ባሻገር ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረትም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት መምህርና ተመራማሪ ሳሙኤል ጂሎ (ዶ/ር) ናቸው።
መንግስት ያቀዳቸውን ተግባራት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የለውጥ ሥራዎች ውስጥ በማካተት በውጤታማነት እንዲተገበሩ የራሳቸውን አስተጽኦ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በግብርናው ዘርፍ የካበተ አቅምና ብቁ ተመራማሪዎች እንዳሉት ሳሙኤል (ዶ/ር) ገልጸው፣ ይህንን በመጠቀም መንግስት በግብርናው ዘርፍ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ምርታማነትን የሚያሳድጉ ምርምሮችን በማድረግ ያግዛል ብለዋል።
ምሁራኑ የመደመር መንግሥት የያዛቸው ግቦች እንዲሳኩ በምርምር፣ በመማር ማስተማርና በማህበረሰብ አገልግሎት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።