ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የዲጂታላይዜሽን አቅጣጫ  ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል

ጅማ  ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ) ፦ የመደመር መንግሥት የዲጂታላይዜሽን  አቅጣጫ  ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅም እንደሚሆን  ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምስረታ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ መንግሥት ከዚህ ቀደም ኢ-ኮደርስ ሥልጠና፣ዲጂታል መታወቂያን ጨምሮ የተለያዩ የዲጂታል ልማት ሥራዎችን ማከናወኑን አንስተዋል።

በኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና የወሰዱ የጅማ ከተማ ወጣቶችም፣ የመንግሥት የዲጂታላይዜሽን አቅጣጫ በተለይ ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል በግሉ  በሶፍትዌር ማበልፀግ  የተሰማራው ወጣት አደም ሰይድ እንዳለው በወሰደው የኢ-ኮደርስ ሥልጠና እውቀትና ክህሎቱን በማሳደግ ወደ ስራ እንዲገባ አድርጎታል።


 

አዲስ የተመሰረተው መንግስትም  የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን ለማስፋፋት የያዘው አቅጣጫ  የወጣቶችን የስራ እድል እንደሚያሰፋው  ተናግሯል።

በመንግሥት አገልግሎቶቹን ዲጂታላይዝ በማድረግ የተገልጋይን ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብ የተዘረጉ አሰራሮች ውጤት ማምጣታቸውን የገለጸችው ደግሞ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሙያ የሆነችው ወጣት ሀናን አሙቲ ናት።


 

በቀጣይም ሥራዎቹን ለማስፋፋት መንግስት የያዘው እቅድ ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን ተደማሪ አቅም እንደሚሆን  ጠቅሳለች።

በኢ-ኮደርስ ሥልጠና ራሷን በማብቃት ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንዳስቻላት የጠቆመችው ደግሞ ሌላዋ የመሶብ አንድ ማዕከል ባለሙያ አሲያ አባፊራ ናት።


 

መሰል የዲጂታል መሰረተ ልማት ሥራዎች የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ለወጣቶች የበለጠ ተደራሽ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ እንደሚያስችል  ገልጻለች።

ሌላው የጅማ ከተማ ነዋሪ መሀመድ ሀይደር በበኩላቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን እቅዶች  የመንግስት አገልግሎት  አሰጣጥን ለማሳለጥ ተግባራዊ የተደረጉ  እንደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያሉ ተቋማት አጋዥ ናቸው።


 

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ መሀመድ ሙንታዝ (ዶ/ር) ፤ የመንግስት የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ለወጣቶች ትልቅ  የስራ እድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።


 

ተግባሩ በቴክኖሎጂ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ትልቅ አቅም በመፍጠር ተወዳዳሪነትን ለማስፋት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ስራዎች ወጣቶችን በዓለም የሥራ ገበያ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው  አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም