ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ያለውን እምቅ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት በማልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ጎንደር ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ) ፦በአማራ ክልል የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ጸጋን በማልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ  ጋሻው ሙጨ (ዶ/ር) ገለጹ።

የቢሮው ኃላፊ  ጋሻው ሙጨ (ዶ/ር)  እንደገለጹት፤በመንግስት ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። 

በክልሉም በዘርፉ ያለውን እምቅ ሀብትና ጸጋ በማልማት ለአገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅትም  ወጣቶችን በዶሮ ፣ በወተት ፣ በማር ፣ በስጋ እና በዓሳ ሀብት ልማት በክላስተር በማደራጀትና ወደ ስራ በማስገባት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል። 

የተገኘውን ተሞክሮ በመጠቀምም በተያዝው በጀት ዓመት በዘርፉ ከ212 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል።

ዘርፉ በትንሽ ቦታ ስራ ለመጀመር  እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል መሆኑን  አመልክተው ፤ ቢሮው የምርት መጠንና ጥራትን ከፍ ለማድረግ  በዝርያ ማሻሻል ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በክልሉ 46 የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በመትከል የእንስሳት መኖ አቅርቦት ችግርን ለመፍታትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።


 

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ምስጋናው ታከለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዘርፉን ከልማዳዊ አሰራር በማውጣት በቴክኖሎጂና በሳይንሳዊ እውቀት የታገዘ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ሼዶችን በመገንባት የወተት፣ የዶሮ ፣ የእንቁላል ፣ የማርና የስጋ ምርቶችን በክላስተር የማልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከዚሁ በተጨማሪም  በዘርፉ ለሚሰማሩ ወጣቶችም የመስሪያ ቦታ፣ የብድርና የግብአት አቅርቦት የማመቻቸት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

"በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ውጤታማ ሆነዋል" ያሉት ደግሞ የሰሜን ጎንደር ዞን እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸጋው ጌታቸው ናቸው።


 

የእንስሳትና ዓሳ ዘርፉን ዘመናዊ ለማድረግም ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ግብርና እንዲሁም እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮዎች "ዘመናዊ ግብርና ለሁለንተናዊ ልዕልና" በሚል መሪ ቃል በጎንደር ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄዱ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም