ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የለማ የሰሊጥ ሰብል እየተሰበሰበ ነው 

ገንዳውኃ ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ) ፦በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማ የሰሊጥ ሰብል እየተሰበሰበ መሆኑን  የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ጌትነት ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በክረምቱ ወቅት የለማውን የሰሊጥ ሰብል ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የመሰብሰብ ስራ እየተካሔደ ይገኛል።

የሰሊጥ ሰብል ለምርት ከደረሰ እንደ ሌሎች የሰብል ዓይነቶች ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ ለብክነት ሳይጋለጥ ፈጥኖ የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩን ነው የገለጹት።

እስካሁን በተደረገው ጥረትም በሰሊጥ ከለማው ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን ለመሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።


 

የሰሊጥ ምርት ስብሰባውን እስከ ጥቅምት 2019 ዓ.ም. ማጠናቀቂያ ድረስ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል።

የሰሊጥ ሰብሉን ለመሰብሰብ በርካታ የጉልበት ሠራተኛ እንደሚጠይቅ የገለጹት የቡድን መሪው፣ ይህም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል። 

በባለሀብቶችና አርሶ አደሮች ዘንድሮ ከለማው የሰሊጥ ሰብል ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

የታጨደው ሰሊጥ በእንስሳት፣ በነፋስና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት ለብልሽት እንዳይጋለጥ ከአጨዳ ጎን ለጎን አራግፎ ወደ ኩንታል የማስገባት ሥራ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።


 

የሰሊጥ ምርቱን በወቅቱ ጥራቱን ጠብቆ በመሰብሰብ ለወጭ ንግድና ለኢንዱስትሪ ግብአት ለማዋል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመተማ እርሻ ልማት በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብት ተወካይ አቶ ሲሳይ ደሴ ፤ ከ20 ሄክታር በላይ በሆነ መሬት የሰሊጥ ሰብል ማልማት መቻላቸውን ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅትም በሰብሉ ከተሸፈነው ውስጥ አራት ሄክታር ላይ የሚገኝ የሰብል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን በዚህም ከ100 በላይ ለሚሆኑ የጉልበት ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

የመተማ ወረዳ ኪኪት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰጠኝ ካሳሁን በበኩላቸው፤ በሰሊጥ ከሸፈኑት ሦስት ሄክታር መሬት 20 ኩንታል  ምርት ለማግኘት እየሠሩ መሆኑን አስረድተዋል። 

በዞኑ በአጠቃላይ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው ከ561 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ከ12 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም