ቀጥታ፡

የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ከመንግስት ጋር በትብብር እንሰራለን 

ሀዋሳ፤ መስከረም 29/2019 (ኢዜአ) ፦ የመደመር መንግስት የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት በሚያከናውናቸው ተግባራት በትብብር እንደሚሰሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሲዳማ ክልል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመንግስት ምስረታ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስተላለፏቸው መልዕክቶችና የቀጣይ የመንግስት ትኩረቶችን በአጽንኦት እንደተከታተሉ ተናግረዋል።

በዚህም በመደመር መንግስት በቀጣይ ለማከናወን የተያዙ አቅጣጫዎችና ግቦች መንግስት በሁሉም ዘርፍ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ በመሆኑ ለተፈጻሚነታቸው በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ዘርፍ ሃላፊ አቶ በለጠ ስጌቦ፤ በመንግስት ምስረታ ቀን የተላለፉ መልዕክቶች መንግስት አካታች በሆነ መልኩ ልማትን ለማፋጠንና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።  

ሰላምና ልማት እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ጨምሮ የተያዙ የመንግስት አቅጣጫዎች ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን አንስተው፣ በተለይ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሰላም አማራጭን አሟጦ ለመጠቀም መንግስት ቁርጠኝነቱን ማሳየቱ ይደገፋል ብለዋል።

የሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ዕድገት ለድርድር አይቀርብም ያሉት አቶ በለጠ፤ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማቸውና የትግላቸው ዋናው ግብ ሀገርን ማልማትና ከፍታዋን ማረጋገጥ መሆኑን አንስተዋል።

መንግስት የሁሉንም ድምጽ ባከበረና አካታች በሆነ መልኩ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ማሳየቱን ገልጸው፣ በቀጣይ የተያዙ አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከመንግስት ጋር ተባብረን እንሰራለን ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተማም ሆነ በገጠር የተመዘገቡ ተጨባጭ የልማት ውጤቶች ተግቶ ከተሰራ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ ናቸው ያሉት አቶ በለጠ፤ የመደመር መንግስት ይህንን በማጠናከር የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ መትጋት አለበት ብለዋል።

በቀጣይ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ልማትን ለማጠናከርና ሙስናን ለመከላከል ሁሉንም ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ ለመስራት የተያዘው ዕቅድም መተግበር እንዳለበት አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሲዳማ ክልል የስልጠናና የክህሎት ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ሀረገወይን ዘሪሁን፤ የመደመር መንግስት ሁሉን አቀፍ የልማት አቅጣጫዎች ለሀገራዊ ልማትና ፈጣን ዕድገት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ መንግስት ያቀዳቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት ተፈጻሚ እንዲሆኑ ተባብረን እንሰራለን ሲሉም ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል። 

ባለፉት ዓመታት በትምህርትና በጤና የታየውን ለውጥ እንዲሁም ግብርናን በማዘመን ከቤት ፍጆታ ባለፈ ትርፍ የማምረት ሥራው መጠናከር እንዳለበት ገልጸው፣ አዲሱ መንግስት ለፍትሀዊ የልማት ተደራሽነት አበክሮ መስራት አለበት ብለዋል።

እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ በሰላምና በልማት እንዲሁም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት ለማስከበር ከመንግስት ጎን ቆመን የሚጠበቅብንን እንወጣለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም