ቀጥታ፡

የላቀች ኢትዮጵያ - የመደመር መንግስት

 

የመደመር መንግስት ምስረታን ተከትሎ ሀገሪቱ ወደ አዲስ የፖለቲካና የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግራትን መንገድ ጀምራለች።

ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ አዲስ መንግስት ከመመስረት ባለፈ አዲስ አቅጣጫና ተስፋን ይዞ መጥቷል።

ይህ ጉዞ ሀገሪቱ ካለፉት ውስብስብ ፈተናዎች ወጥታ ወደ ላቀ የስልጣኔ ማማ፣ ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለመሻገር ያላትን ፅኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

አዲሱ መንግሥት ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በነፃና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሰጡት ድምፅ ላይ የቆመ መሆኑ፣ ከሕዝብ ጋር ያለውን ማህበራዊ ውል በአዲስ መልክ ያደሰበት የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ተደርጎም ይወሰዳል።

ይህ አዲስ አቅጣጫ የሕዝብን የነገ ብሩህ ተስፋ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት እንዲሁም የልማትና እድገት ስኬቶችን በላቀ የውጤታማነት ደረጃ ለማስቀጠል የተቀረፀ ታላቅ ራዕይ ነው።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሰላምና ጸጥታን ይበልጥ ማጽናት፣ የባህር በር ባለቤት መሆን፣ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግሩን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ፣ የማህበራዊ ልማትና ጥበቃ ሥራዎችን ማጠናከር እንዲሁም መሠረተ ልማትን ማስፋፋት የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

የተያዙት እቅዶች በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን ይበልጥ ለማጠናከር፣ ተቋማዊ አቅምን ለማጎልበት እና የዜጎችን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ናቸው።

አዲሱ መንግሥት ለገበያ መረጋጋት፣ ለቤት አቅርቦት እና ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ዕድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተመልክቷል።

የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጠርባቸውን መስኮች በማስፋፋት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ ትልቁ የቤት ሥራ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሹመታቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ጠንካራና አይበገሬ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ስርዓት እየገነባች ያለች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

ማንኛውም የውስጥና የውጭ ፈተና የሀገሪቱን የሥልጣኔና የብልጽግና ጉዞ ሊያቆመው አይችልም ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የያዘቻቸውን ታላላቅ እቅዶች እውን ለማድረግ የመንግሥትና የሕዝብ  ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሄንን ታላቅ ርዕይ እውን ለማድረግ ያስችላቸው ዘንድ በህዝብ ድምጽ የተመረጠውና አደራንም የተረከበውን መንግስት ካቢኔ በአዲስ መልክ አደራጅተዋል።

የሃገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድሙ ለህዝብ ተጠቃሚነት ያለድካም በትኩረት የሚሰሩና በጥብቅ ዲሲፕሊን የተመረጡ አባላትን በማደራጀትና ሹመታቸውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማስጸደቅ ስራ ጀምረዋል።

ከአመራሩ ባለፈ ደግሞ ዜጎችም በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ተመልካች ብቻ ሳይሆኑ የለውጡ ባለቤት በመሆን፣ የላቀች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ይጠበቃል። መሆንም አለበት።

ይህ አዲሱ የመንግሥት ምሥረታና ግዙፍ ሀገራዊ ትልሞች፣ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ የሥልጣኔና የብልጽግና ምዕራፍ ለማሻገር መሰረት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም