ቀጥታ፡

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ፤ የመደመር መንግሥት ገለልተኛ ተቋማት ግንባታ ተጨባጭ ፍሬ!!

ምርጫ የሥልጣን ማሸጋገሪያ፣ የዜጎች የፖለቲካ ይሁንታ ችሮታና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ በተግባር የሚፈተንበት የአደባባይ መድረክ ነው። በዚህ ሂደት የዜጎች ተሳትፎ፣ የተቋማት አቅምና የፖለቲካ ተዋናዮች የፉክክር ልምምድ በጋራ ሲጣመሩ የሀገርን የዴሞክራሲ ግንባታ ያጎለብታል።

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጤናማ ፉክክር ማዕከል ያደርጋል። የፉክክር ሂደቱም በሕግ፣ በተቋማት ግንባታና በዜጎች የነቃ ተሳትፎ እየፈካ የሚሄድ የዴሞክራሲ ልምምድ ነው።

ይህም በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ-8 ንዑስ አንቀጽ-3 ላይ የሕዝቦች ሉዓላዊነት በተመረጡ ተወካዮችና በቀጥታ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የሚገለጽ መሆኑን ይደነግጋል። በተመሳሳይም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ-38 ንዑስ አንቀጽ-1 (ሀ) መሰረት ዜጎች በቀጥታና በነፃ በመረጧቸው ተወካዮች በኩል በሕዝባዊ ጉዳዮች አስተዳደር የመሳተፍ ሙሉ መብት አላቸው።

ምርጫ የሥልጣን ማሸጋገሪያ መንገድ፣ ዜጎች የፖለቲካ ፈቃዳቸውን የሚገልጹበት፣ ተቋማት የዴሞክራሲ አሰራራቸውን የሚፈትኑበትና ከሂደቱ የሚገኘው ልምምድ ለቀጣይ የዴሞክራሲ ግንባታ መሠረት የሚሆንበት የአደባባይ መድረክ ነው።

ከዚህ አንጻር የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ በመግለጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተሞክሮዎችንና የተቋማትን አቅምን የሚያሳይ የአስቻይ ልምምድ ሆኖ አልፏል።

በሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የዴሞክራሲ ባህል የሚፈተነው በምርጫ ወቅት በሚካሄድ ልምምድ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም እንደማንኛውም ሕዝባዊ ምርጫ ተካሄደ ተብሎ ብቻ የሚገለጽ የሰርክ ክንውን እንዳልነበረ በመጠቆም፤ ዜጎች ፈቃዳቸውን ለመግለጽ በብዙ ውዥንብሮች መካከል ማለፋቸውን አንስተዋል።

የምርጫው አጠቃላይ ሂደትም የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ መሰረቱ እየጠነከረ መምጣቱን በግልጽ በማሳየት ወደፊት ታሪክ በደማቅ ብዕር እንደሚጽፈውና ትውልድም ደጋግሞ እንደሚዘክረው ገልጸዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ምርጫን ከአንድ የሥልጣን ውድድር ባሻገር የዴሞክራሲ ልምምድን ለማጠናከር የሚያልፍበትን ሂደት በጉልህ ያመላክታል።

በኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች በመሳተፍ ዜጎች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት በተግባር አስመስክረዋል።

የኢትዮጵያውያን በምርጫው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከሌሊት እስከ ሌሊት ያሳዩት ቁርጠኝነት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ቀናኢነት በግልጽ አሳይተዋል።

ይህም ዜጎች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሩቅ ተመልካች ሳይሆኑ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም በሂደቱ ውስጥ በቀጥታ የሚሳተፉ ባለቤቶች መሆናቸውን አረጋግጧል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የወጣቶች ተሳትፎም የኢትዮጵያ ወጣቶች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና በተግባር አንጸባርቋል።

ወጣቶች በመራጭነት፣ ተመራጭነት፣ በአስተባባሪነትና አስፈጻሚነት የነበራቸው ንቁ ተሳትፎም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አካል መሆናቸውን አንጸባርቋል።

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም የቅድመ ምርጫ፣ ምርጫና የድህረ ምርጫ ሂደት ውጤታማነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የገለልተኛ ተቋማት የማስፈጸም አቅም እየጎለበተ መምጣቱን ልብ ይሏል።

ምርጫ በተፈጥሮው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃሳብ ጠረጴዛ ተገናኝተው የሚፎካከሩበት ሂደት ሲሆን በመጨረሻ ሀገር አሸናፊ የምትሆንበትን አማራጭ በጸጋ የሚቀበሉበት ስልጡን መድረክ ነው።

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን ስብሰባ ላይ፤ ማንኛውም ምርጫ አሸናፊና ተሸናፊ ፓርቲ ሊኖረው ቢችልም ኢትዮጵያ ግን አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ዜጋ እንደማይኖራት መናገራቸው።

የምርጫ ሂደት የሚመዘነው በአሸናፊና ተሸናፊ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ዜጎች የፖለቲካ ፈቃዳቸውን በሕጋዊ መንገድ መግለጽ መቻላቸውና ተቋማት ሂደቱን በአግባቡ መምራታቸው ጭምር ነው።

የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ በአንድ ምርጫ ሂደት የሚጠናቀቅ አይደለም። ይልቁንም የዜጎች ተሳትፎ፣ የወጣቶች ሚና፣ የፖለቲካ ተዋናዮች ልምምድና የምርጫ ተቋማት አቅም በተከታታይ ሲጠናከር የሚገኝ ውጤት እንጂ።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከውጤት ባሻገር በዜጎች ተሳትፎ፣ በወጣቶች ሚና፣ በመንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተቋማዊ ልምምድ የተገኙ ተሞክሮዎችን ለቀጣይ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዋል ላይ ይመሰረታል።

የመደመር መንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛነት የሚያስጠብቅ ውጤታማ የሪፎርም እርምጃ ውስዷል። ፍሬውም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማስፈጸም አቅም በተግባር ታይቷል። ዜጎችም ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን በማካሄድ መንግሥታቸውን እንዲመሰርቱ አስችሏል።

የምርጫ ቀን ሲያበቃ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የሚያበቃ አይደለም። የተገኘውን ልምድ ወደ ቀጣዩ ምርጫ፣ ወደ ቀጣዩ ትውልድና ወደ ቀጣዩ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ምዕራፍ እየተላለፈ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም