ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር ጠንካራ የፖለቲካ ባህል እያጎለበተ ነው 

አዲስ አበባ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር እሳቤ ለኢትዮጵያ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ የከፈተና አገራዊ ጥቅምን በሚያስተማምን ሁኔታ የሚያስከብር  ጠንካራ የፖለቲካ ባህል እያጎለበተ መምጣቱን ምሁራን ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሰይመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፤ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪዎች በአንድ መንግሥት ውስጥ ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መስራት እንደሚቻል በተግባር መረጋገጡንና ይህም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እያጠናከረው መምጣቱን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ሄኖክ ስዩም (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የመንግሥት ምሥረታ ሂደቱ የዴሞክራሲ ባህልና የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ፍሬ ማፍራት መጀመሩን የሚያሳይ ነው።

መንግሥት በግብርና፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪና ታዳሽ ኃይል ላይ ትኩረት በማድረግ የኢኮኖሚ እድገቱን እያፋጠነ ይገኛል ብለዋል። 

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የባህር በር መብት እንዲሁም ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክር አቋም መያዙ ሀገራዊ አንድነትን ያጎለበተ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት አቅጣጫ መቀመጡም ለሰላም ስኬት ትልቅ ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል።

በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አብዱበሽር ሰይድ በበኩላቸው፤ የዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ የፖሊሲ አቅጣጫዎች መቀመጣቸው የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚረዱ አዎንታዊ እርምጃዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተጀመሩ የልማትና የሰላም ስኬቶች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ምሁራን በምርምር የተደገፉ የመፍትሔ ሃሳቦችን በማቅረብ፣ መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊ መረጃ በማሰራጨት እንዲሁም ህዝቡ ልማትና ሰላምን በመንከባከብ የተቀናጀ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም