ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የማይታለፍ ቀይ መስመር - ሙስና ሌብነትና የወገንተኝነት አሰራር!!

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ሙስና፣ ሌብነትና ወገንተኝነት የሀገርን ዕድገትና ብልፅግና ያኮሰምናል። የዜጎችን ፍትሐዊና ግልጸኝነት የሰፈነበት የአስተዳደር ሥርዓት መሻት የሚገዳደር የልማት ጠንቅም ነው። ለዚህም ነው የመደመር መንግሥት ጠንካራ አቋም የያዘው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ ዳግም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሰየሙበት ወቅት፤ ሙስናን፣ ሌብነትን፣ የዘመድ አሰራርንና ወገንተኝነትን ለማስወገድ መንግሥት መራር እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስምረውበታዋል።

ይህ የመደመር መንግሥት ግልጽ አቋም ሌብነትና ሙስና የማይታለፍ ቀይ መስመር መሆኑን ያሳያል። መልዕክቱም የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶችን በማዘመን ብልሹ አሰራርን ለመግታትና ለሙስና መንስኤ የሆኑ ክፍተቶችን ለመዝጋት ትኩረት እንደሚሰጡ ያመላክታል። ይህም ለዜጎች ተስፋ፣ ለሙሰኞች ደግሞ መርዶን የሚያሰማ ጥብቅ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው።

አንድ ዜጋ የመንግሥት አገልግሎት ሲፈልግ ከቢሮ ቢሮ መዞር፣ ረጅም ወረፋ መጠበቅ፣ የግለሰብ ግንኙነትን ማማተርም ሆነ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ መጠየቅ የለበትም። የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እንዝህላልነት ሙስናን፣ ወገንተኝነትንና የዘመድ አዝማድ አሰራርን ያበረታታሉ። የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያወጣው የሦስተኛው ብሔራዊ የሙስና ግንዛቤ ጥናትም በሙስና፣ በሌብነትና በብልሹ አሰራር ላይ ተከታታይና መራር እርምጃ የመውሰድ አስፈላጊነትን ያመላክታል።

የመደመር መንግሥት ይህን ክፍተት ለመዝጋት የዲጂታል አብዮትን እንደ ዋና መሣሪያ የሚጠቀም ዘመናዊ የአገልግሎት ምኅዳር እየፈጠረ ይገኛል። ለዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥርዓት ተጨባጭ አብነት ነው። የተቋማት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል መቅረባቸው ዜጎች ከቢሮ ቢሮ መዞር ሳይጠበቅባቸው የአገልግሎት ሂደቱን ግልጽና ፈጣን ያደርገዋል።

በፌዴራል ደረጃ የተጀመረው የመሶብ አንድ ማዕከል የዲጂታል አገልግሎት ምኅዳርም አሁን ላይ የተደራሽነት አድማሱን አስፍቷል። ለአብነትም በአዲስ አበባ በ2018 ዓ.ም ብቻ በ11 ክፍለ ከተሞች የመሶብ የዲጂታል አገልግሎት ማዕከላት ወደሥራ ገብተዋል። አሁን ይህ ሥርዓት ወደ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እየተስፋፋ ይገኛል። ከዚህም በላይ በተንቀሳቃሽና በእጅ ስልክ መተግበሪያ የተቀናጀ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ዜጎች በቤታቸውና በአቅራቢያቸው እንዲገለገሉ አስችሏል።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያም የዚህ ጉዞ ወሳኙ አካል ሆኗል። አንድ ሰው አንድ ነው በሚል የተጀመረው መርሃ ግብሩም የግለሰብን የዲጂታል መለያ በማረጋገጥ የሐሰት ሰነድና የማጭበርበር ዕድልን በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል። የተቀናጀና የተናበበ አገልግሎትን ለዜጎች በመስጠትም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ማስገኘቱን ቀጥሏል።

የዲጂታላይዜሽን ጉዞው የመንግሥት አገልግሎትን ከግለሰብ ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆን አድርጓል። የዲጂታል አገልግሎቶች ግልጽነትን በማስፈን ተጠያቂነትን እያረጋግጡ ነው። የዲጂታል ግብይትና ክፍያ ሥርዓት መስፋፋቱም ተመሳሳይ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የአገልግሎት ምኅዳር ዕድልን ፈጥሯል። የገንዘብ ዝውውርና እንቅስቃሴ የግብይት ሥርዓት ከእጅ ንክኪ በጸዳ ቁጥር የሙሰኞችን ሸምቀቆ በማጥበቅ ተጋላጭነትን መቀነስ ያስችላል። ይህም የመደመር መንግሥት የዲጂታል አብዮት አንዱ ተጨባጭ እመርታ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ የተጀመረውን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በማጠናከር የአገልግሎት አሰጣጥን የበለጠ ለማዘመን ትኩረት ይሰጣል። ብቃት ላይ የተመሠረተ የሥራ መመዘኛና የአፈጻጸም ክትትልም ሙስና፣ ሌብነት፣ የዘመድ አሰራርና ወገንተኝነትን የሚያከስም ሁነኛ መሠረት ነው። እነዚህ እርምጃዎችም የመደመር መንግሥት ሙስናን ከወንጀለኛ መቅጣት ባሻገር ሌብነት እንዳይፈጠር የሚያደርግ ሥርዓት ለመገንባት የሚያከናውነውን ተከታታይ ተግባር ያመላክታል።

ይህን ቁርጠኝነት ወደ ተግባር ለመቀየርም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ተከታታይ ሥራ እየሰራ ይገኛል። ኮሚቴው የሙስና፣ የሌብነትና የወገንተኝነት ትግልን በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ በመምራት በሌብነት ላይ የሚወሰደውን መራር እርምጃ በሥርዓት እያስፈጸመ ነው።

መራር እርምጃው ቃል ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ ለውጥ መሆን አለበት። የፀረ-ሙስና ተቋማት አቅም፣ የሲቪል ሰርቪስ ብቃት፣ የዲጂታል አገልግሎት ስፋት፣ የመንግሥት ግዥ ግልጽነትና የፕሮጀክት ክትትል በአንድ ላይ ሲሰናሰሉ የሚለካ ውጤት ይመጣል። የመደመር መንግሥት ጽኑ ፍላጎትም ለዜጎች ያለአንዳች እጅ መንሻና ብልሹ አሰራር የመንግሥት አገልግሎት ማስገኘት ነው። ዜጎች በየቀኑ በመንግሥት ተቋማት የሚያገኙት ፍትሐዊና ግልጽ አገልግሎትም ሌብነትን የሚያደርቅ እውነተኛ መለኪያ ይሆናል።

ትልቅ ሀገርና ትልቅ ሕዝብን የሚመጥን ታላቅ ርዕይ ለሰነቀችው ኢትዮጵያ ርዕይን በተግባር የሚያስፈጽም ታማኝ፣ ብቁ፣ ግልጽና ተጠያቂ ተቋም እየተገነባ ነው። የመደመር መንግሥት ሙስና፣ ሌብነትና ወገንተኝነትን የማይታለፍ ቀይ መስመር አድርጎ መበየኑም የሀገርንና የሕዝብን ሀብት ለተፈለገው ዓላማ ለማዋል ካለው ቁርጠኛ አቋም ይመነጫል።

የፍትሐዊ የመንግሥት አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትም ለዜጎች ተስፋን፣ ለሌቦች ደግሞ መርዶን የሚያውጅ ጥብቅ የማስጠንቀቂያ ደወል ሆኗል። የሌብነት ቀይ መስመርነትም የሕዝብና መንግስትን መተማመን በማጎልበት የኢትዮጵያን መሻት በማላቅ ዕድገትና ብልፅግና ለማሳለጥ ተስፋን የፈነጠቀ ቀጣይነት ያለው ሥራ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም