የአፈር ለምነትና ጤንነትን ለመመለስ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት እያሻሻሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፈር ለምነትና ጤንነትን ለመመለስ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት እያሻሻሉ ነው
አዲስ አበባ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦የአፈር ለምነትና ጤንነትን በመመለስ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማሻሻላቸውን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ፈቃዱ ጉርሙ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከኮሪያ ዓለም አቀፍ የግብርና ፕሮጀክት (KOPIA) ጋር በመተባበር የአፈርን ለምነትና ጤንነት በመጠበቅ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ የሦስት ዓመት ፕሮጀክት እየተገበረ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዛሬው ዕለት ፕሮጀክቱ እየተተገበረ በሚገኝበት በቢሾፍቱ አካባቢ ደንካካ ቀበሌ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችና የለሙ ሰብሎች የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ፈቃዱ ጉርሙ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በየጊዜው የሚያወጣቸው ልዩ ልዩ የሰብል ዝርያዎች የግብርና ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን እያሳደጉ ይገኛሉ።
ቀደም ሲል ከ KOPIA ጋር በሰብል ማልማትና በዝርያ ማሻሻል ላይ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ትኩረቱን አፈር ላይ ያደረገ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
አፈር አስፈላጊውን ንጥረ ነገር አግኝቶ ጤንነቱ ሲጠበቅ ከፍተኛ ምርትና ምርታማነትን ይሰጣል ብለዋል።
አፈር ታመመ የሚባለው ሰብል ሊሰጠው የሚገባውን ንጥረ ነገር መስጠት ሲያቅተው፣ የንጥረ ነገር ይዘቱ ሲቀንስ፣ አሲዳማና ጨዋማ ሲሆን፣ እንዲሁም ውሃ አፈሩ ላይ በመተኛቱ ምክንያት ሰብሎች ተስፋፍተው እንዳይበቅሉ ሲያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የአፈርን ለምነት በመመለስ የአርሶ አደሩን ምርታማነት እያሻሻሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የኮሪያ ዓለም አቀፍ የግብርና ፕሮጀክት (KOPIA) የኢትዮጵያ ማዕከል ዳይሬክተር ሶንግ ዮንግ፤ ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ያላቸውን ታሪካዊ ወዳጅነት አሁን ላይ በግብርና ትራንስፎርሜሽን እና በቴክኖሎጂ ሽግግር በማጠናከር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የአፈርን ኦርጋኒክ ይዘት በመገንባት፣ የውሃ ፍሳሽ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በማስፋፋት እንዲሁም የመኖ ሰብሎችን በማልማት የእንስሳት መኖ አቅርቦትንና የሰብል ምርታማነትን ያቀናጀ አሰራር እንደሚተገበር ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቱ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከቢሾፍቱ ምርምር ማዕከል እና ከኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የምርምር ውጤቶችን በቀጥታ ለአርሶ አደሩ የማድረስ ሥራ እንደሚሠራም አስረድተዋል።
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ በአፈር ለምነትና ጤንነት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ምርትና ምርታማነታቸውን እንዳሳደገላቸው አረጋግጠዋል።