ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ፈጠራን ከምርታማነት ጋር ለማስተሳሰር እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ፈጠራን ከምርታማነት ጋር ለማስተሳሰር እየሰራ ነው
ባህር ዳር፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ችግር በምርምር ለመፍታትና ፈጠራን ከምርታማነት ጋር ለማስተሳሰር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው 3ኛውን ዓመታዊ የማህበረሰብ ተሳትፎና የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር አውደ ጥናት ዛሬ አካሂዷል።
በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር እንየው አድጎ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማርና ከምርምር ሥራው ባሻገር ለማህበረሰብ አገልግሎት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
የፈጠራና ምርምር ሥራ የሚያከናውኑ ኢንዱስትሪዎችና ተመራማሪዎችን በመደገፍ የማምረትና የአገልግሎት አሰጣጥ አቅምን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማብዛት፣ የኢንዱስትሪ አጋርነት፣ የምክር አገልግሎትና የፋይናንስ ተደራሽነት ላይ ይበልጥ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የዛሬው አውደጥናትም ከልምድ ልውውጥ ባሻገር ምርምርን ወደ ቁሳዊ ሀብትና አገልግሎት ለማሸጋገር የሚያስችሉ የጋራ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑ አስረድተዋል።
የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ በተለያዩ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ችግሩን መሰረት ያደረገ የምርምር ሥራ ማከናወን ወሳኝ ነው።
በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት የጀመረው የምርምር ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ይህም ችግሮችን ወደ መልካም ዕድል በመቀየር የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአማጋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መጣአለም አማረ እንደገለጹት፤ ወጣት ተመራማሪዎች የሚያካሂዱት የምርምር ሥራ በፋብሪካው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችል ነው።
በአውደጥናቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የክልልና የፌዴራል የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።