ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን መሻት የሚያሳካ- የመደመር መንግሥት  

በሰውነት ጀምበሩ

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል በተለያዩ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓቶች ያለፈች ጥንታዊት ሀገር ነች። ይህ የመንግሥት ሥርዓተ ታሪክ የመሪዎችን ርዕይ፣ የሕዝቦችን አብሮነት፣ የሥልጣን ፍላጎትና የሀገር ግንባታ ሕልምን አጣምሮ የያዘ ሕያውና የዘመናት ጉዞ ነው።

የኢትዮጵያ ታሪክ ከንጉሠ ነገሥቱ ፍጹማዊ ማዕከላዊነት ጀምሮ እስከ ደርግ ሶሻሊስታዊ ሙከራ፣ ከኢሕአዴግ የብሔር ፌዴራሊዝም እስከ አሁኑ ሀገር በቀል የመደመር ፍልስፍና ያለው ሂደት እያንዳንዱ ሥርዓት በሀገሪቷና በሕዝቦች ላይ የራሱን ዐሻራ አሳርፏል፤ እያሳረፈም ይገኛል።

የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በዘመናዊ ተቋማት ግንባታና በማዕከላዊ ጠንካራ መንግሥት ምስረታ የሚታወስ ቢሆንም የሰፊውን ሕዝብ መሠረታዊ የነፃነት፣ የመሬት ባለቤትነት እና የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ በለውጥ ማዕበል ተናግቶ በደርግ ወታደራዊ ሥርዓት ተተካ። ደርግ "መሬት ላራሹ" አዋጅን የመሳሰሉ ጅምሮችን ቢያደርግም፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመርገጡ እና የቀይ ሽብርን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማካሄዱ ኢትዮጵያን ረጅም የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከቷታል።

ደርግ የ1987 ዓ.ም ሕገ-መንግሥት ሀገሪቱን በብሔር፣ በቋንቋና በመልክዓ ምድር ላይ በተመሠረቱ 9 ክልሎችና 2 የከተማ አስተዳደሮች በመክፈል አስተዳደራዊ መዋቅሩን ዘረጋ። ይሁን እንጂ ጠንካራ የሕዝብ አገልግሎት ፍላጎት የሚያረካ፣ ለልማትና ለዕድገት ቅድሚያ የሚሰጥ ተቋም መገንባት ተስኖት ቆይቷል።

በእርግጥ የኢሕአዴግ በሕገ-መንግሥት አስተዳደር ለዘመናት ታፍነው የነበሩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋቸውን እንዲያደራጁ፣ ባህላቸውን እንዲያሳድጉና አካባቢያቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን ዕድል ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ነገር ግን የፖለቲካ ምኅዳሩን አንዱን አጋር ሌላውን እህት በሚል አግላይና ከፋፋይ ስልት አስተዳደር የዘረጋው ሕወሓት መራሹ ሥርዓት በሀገሪቷ ላይ ፈላጭ ቆራጭ በመሆን ሥልጣነ መንበሩን ተቆናጦ ቆይቷል።

ይህም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ሰዎችን ከሀገራዊ ዜግነታቸው ይልቅ በብሔር አጥር ውስጥ ብቻ እንዲወሰኑ አድርጎ ቆይቷል። የፖለቲካ ምኅዳሩን በመዝጋት፣ የዜጎችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች በመጨቆንና በየአካባቢው የብሔር ግጭቶች እንዲባባሱ በማድረጉ ተቃውሞ ገጠመው። አልቻለም እንጂ የሕዝብን ተቃውሞ በማፈን ለጥቂት ጊዜ ለመራመድም ሙከራ አድርጎ ነበር።

ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ማዕበሉም በአራቱም አቅጣጫ ገደፉን አልፎ ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም ለውጥን አምጣ ወልዳለች። ይህ ለውጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራውን የመደመር መንግሥትን እንዲተዋወቅ አድርጓል። ይህ በሀገር በቀል ዕውቀት የሚመራው የመደመር መንግሥት ስብራቶችን የመጠገንና አዲስ አቅጣጫ የመቀየስ ባሕሪ የነበሩ ጭቆናዎችን በማስቀረት፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን በመቀየር አጋርና ዋና የሚለውን ሥርዓት በማስቀረት ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ላይ የመወሰንና የመጠቀም መብትን የሚያጎናጽፍ ሥርዓት ፈጥሯል።

ዛሬ "መደመር" የሚለውን ሀገራዊ ፍልስፍና መሪ ፍኖት አድርጎ በመውሰድ የመደመር ዕይታ እያሰረጸ መልካም ነገሮችን ማስቀጠል፣ የተበላሹትን ማረምና አዳዲስ የጎደሉ ነገሮችን ማሟላትን እንደ ዋና መርህ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመርን አስተሳሰብ ሲያብራሩ "መደመር ማለት ያለንን መልካም ነገር አቀናጅተን፣ የጎደለንን ሞልተን፣ የተበላሸውን አርመን ወደፊት መራመድ ነው። በጽንፈኝነትና በከፋፋይ ፖለቲካ ሀገር አትገነባም። ኢትዮጵያ ሁላችንንም አቅፋ የምትይዝ ሀገር ናት" ብለዋል።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የለውጥ መንግሥት ኢትዮጵያን ከተረከበ ወዲህ ባለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሁሉን አቀፍ ለውጦች አስመዝግቧል። ለአብነት ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ ኢኮኖሚው ከነበረበት ስብራት የሚያገግምበትን ዕድል ፈጥሯል። ይህም ግብርና መር የነበረውን የኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ ብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫን በመቀየስ በርካታ ለውጦችን አስመዝግቧል።

ባለፉት ዓመታት በርካታ ሀገራዊ ንቅናቄዎች በመተግበር በየዘርፉ እመርታዊ ውጤቶች የሚመዘገብበትን መንገድ ቀይሷል። ይህም ከገበታ ለሸገር ጀምሮ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ በሚል የተፈጠሩ ንቅናቄዎች የቱሪስት መስህቦችና መዳረሻዎችን በማስፋፋትና በማደስ ኢትዮጵያን የቱሪዝም ማዕከል እያደረጋት ይገኛል። ዜጎች የተትረፈረፈና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የሚያስችል የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ተግባራዊ በማድረግ ብዙዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ከራሳቸው አልፎም ለገበያ በማቅረብ ትሩፋታቸውን አጋርተዋል። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ፣ በመሶብ የአንድ ማዕከልና ሌሎችም የተጀመሩ ንቅናቄዎች በርካታ ለውጦችን መመዝገብ ችለዋል።

ለውጡ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስም ከተቃዋሚነት ወደ ተፎካካሪነት በመቀየር በፖለቲካው መስክ ሁሉም እኩል እንዲሳተፍ በማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩን አስፍቷል። በዚህም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ጉዳይ ላይ እኩል የሚሳተፉበትን አውድ ፈጥሯል።

ለዚህም ነው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በርካታ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰላማዊና የተረጋጋ ተሳትፎ ያደረጉት። ሕዝብ የሰጣቸውን ድምፅ ተቀብለው ለሀገር መጽናት በአብላጫ ድምፅ ካገኘው ፓርቲ ጋር በጋራ ለመሥራት ጽኑ አቋማቸውን በመግለጽ በኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አርዓያ የሚሆን ገድል የፈጸሙት።

በሀገር ደረጃ የተመዘገቡትን ድንቅ ለውጦች በጥሞና የተመለከተው ሕዝብ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለብልፅግና ፓርቲ ድምፅ በመስጠት አድናቆቱን ገልጿል፤ ተግባሩንም እንዲቀጥል አደራ ሰጥቷል።

በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ገዥው ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮችን ምክር ቤት 428 ወንበሮችን በማሸነፍ ቀሪዎችን ደግሞ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምፅ አግኝተው ምክር ቤት ገብተዋል። ከአብላጫው ሕዝብ ድምፅ ያገኘውና አደራውን የተቀበለው ብልፅግና በጠንካራ መንፈስ፣ በጸና አደራ የመደመር መንግሥትን መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ መስርቷል።

ምክር ቤቱም በአካሄደው ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰይሟል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሰየሙበት ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥርዓትን የመገንባት ሙከራዎች የቁጭት ችግር ባይኖርባቸውም የእፎይታና የስክነት ችግር ይስተዋልባቸው ነበር።

ባለፉት ዓመታት የሌሎችን ተሞክሮ ከራሳችን ጋር ስናስማማ ቆይተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ መደመር የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ መሆን እንደሚችል አረጋግጠናል ብለዋል። 

አዲሱ የመደመር መንግሥት መጪውን ዘመን ታሳቢ ያደረገ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላት ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር በመቀየር በምክር ቤቱ አዋጅ እንዲጸድቅ አድርጓል። የአዋጁ መውጣትና ተግባራዊ መሆን የተቋማትን የማስፈጸም አቅም ያጎለብታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን አቅርበው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያሾሙ እንደገለጹት፤ ትምህርት ብቻውን የመፈጸም አቅምን ሊተካ ስለማይችል፣ የተማሩ ነገር ግን ተግባር ላይ ውጤት የማስመዝገብ፣ የመከታተልና ከፍተኛ ዲሲፕሊን ያላቸውን ግለሰቦች ማጣጣም ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት የአሁኑ ሹመት ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልክ ከባድ ኃላፊነት ነው። ሌት ተቀን በመሥራት የሕዝብን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ለውጡ በእያንዳንዱ ሰው ዘንድ ጥቅም የሚያስከትል መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ይህ ሲታይ የመደመር መንግሥት ተሿሚዎቹ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሚችሉ በተሰማሩበት የሥራ መስክ የተሻለ አፈጻጸምና ውጤት ያስመዘገቡ አካላት በሥራ ልምዳቸው ተመዝነዋል።

የመደመር መንግሥት ተሿሚዎችም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በርካታ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረትና ሩጫ የሚጠይቅ በመሆኑ ያንን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል አቅም ያላቸው መሆኑ በሚገባ ተፈትሿል። በዚህም በምርጫው ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድምፅ በመስጠት የሰጡትን ታላቅ አደራና የመንግሥትን ቁመና የማጠናከር ፍላጎት ለመሸከም ዝግጁ የሆኑ ሙስናን የሚጸየፉና ሕዝብን ማገልገል እንደ ታላቅ ጸጋ የሚቆጥሩ መሆናቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩም በምክር ቤት አባላትም ታምኖባቸዋል።

ይህ አዲስ አደረጃጀትም የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ የሚረዳ ፍኖት ነው። ነገር ግን ይህ የመንግሥት አደረጃጀት እንደ ሀገር የታሰበውን ሀገራዊ ዓላማ ማሳካት እንዲችል ሁሉም የማኅበረሰብ አካል በየተሰማራበት መስክ መትጋት ይገባል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ ለሁለቱም ምክር ቤቶች ባቀረቡበት ወቅት፤ የኢትዮጵያን ሰላም ለማጽናትና ልማትን ለማረጋገጥ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። እናም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የበኩላችንን ኃላፊነት እንወጣ- መልዕክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም